በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አብን፥ የአቶ ግርማ የሺጥላ ግድያ “የተጠያቂነት አለመኖር ክትያ ነው” አለ


አብን፥ የአቶ ግርማ የሺጥላ ግድያ “የተጠያቂነት አለመኖር ክትያ ነው” አለ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:36 0:00

በዐማራ ክልል የገዥው ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ግርማ የሺጥላን ጨምሮ የአምስት ሰዎች መገደል፣ ከዚኽ ቀደም በክልሉ አመራሮች ላይ ግድያ የፈጸሙ ሰዎች ተጠያቂ አለመኾናቸውን ተከትሎ የመጣ ጥቃት እንደኾነ፣ የዐማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን አስታወቀ።

ገዥው ፓርቲ ብልጽግና በበኩሉ፣ ምልአተ ሕዝቡን ያሳተፈ ጠንካራ የፖለቲካ ትግል በማድረግ፣ ሕግ የማስከበር ርምጃዎችን በማጠናከር ጽንፈኝነትን ለመግታት፣ ከምንጊዜውም በበለጠ ጠንክሮ እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡

አቶ ግርማ የሺጥላ፣ ካለፈው ዓመት መስከረም ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በጽ/ቤት ሓላፊነት የመሩት የዐማራ ብልጽግና ፓርቲ ደግሞ፣ ዛሬ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ በአሰፈረው መልእክቱ፥ የታጠቁ ጽንፈኛ ኃይሎች ያላቸው አካላት፣ ትላንት በአደረሱት ድንገተኛ ጥቃት ከሞቱት ውስጥ፥ የአቶ ግርማ ሹፌር የነበሩት ልየው መንጌ እና አጃቢዎቻቸው እንደሚገኙበት አረጋግጧል።

ትላንት ኀሙስ፣ ሚያዝያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ተወልደው በአደጉበት ሰሜን ሸዋ መሀል ሜዳ የተገደሉትን የዐማራ ክልል የገዥው ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሓላፊ የአቶ ግርማ የሺጥላን ግድያ የሚያወግዙ መግለጫዎች፣ ከልዩ ልዩ ተቋማት እየወጡ ነው።

የዐማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(ዐብን) የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ ጣሂር መሐመድ ከዚኽ ቀደም በክልሉ የተፈጸመው ወንጀል ተሸፋፍኖ መቆየቱ፣ ዐዲስ ወንጀል እንዲፈጸም የሚገፋፋ ኾኗል የሚል አቋም አንጸባርቀዋል።

አቶ ጣሂር በክልሉ መንግሥት አመራሮች ላይ ተደጋግሞ እየተፈጸመ ያለው የግድያ ጥቃት፣ ክልሉን የቀውስ ማዕከል በማድረግ ሕዝቡን ለጸጥታ ስጋት እንደዳረገው ጠቅሰዋል። ከአምስት ዓመት በፊት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የነበሩትን ዶክተር አምባቸው መኮነንን ጨምሮ የአራት ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች በተመሳሳይ መልኩ መገደላቸውንም አስታውሰዋል።

የክልሉን መንግሥት መግለጫ ይፋ ያደረገው የዐማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሚያዝያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሰሜን ሸዋ ዞን መንዝ ጌራ ምድር ወረዳ(መሀል ሜዳ) ወደ ደብረ ብርሃን በመመለስ ላይ ሳሉ መንዝ ጓሳ በተባለው አካባቢ፣ በግል ጥበቃዎቻቸው እና በቤተሰቦቻቸው ላይ፣ “ኢመደበኛ” ሲል በጠራቸው ታጣቂዎች ጥቃት፣ አቶ ግርማን ጨምሮ አምስት ሰዎች መገደላቸውን ይፋ አድርጎ ነበር።

የዐማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ዛሬ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መልእክቱ፣ የታጠቁ ጽንፈኛ ኃይሎች ያላቸው አካላት፣ ትላንት በአደረሱት ድንገተኛ ጥቃት ከሞቱት ውስጥ፥ የአቶ ግርማ ሹፌር የነበሩት ልየው መንጌ እና አጃቢዎቻቸው እንደሚገኙበት አረጋግጧል።

ብልጽግና ፓርቲ በአወጣው የኀዘን መግለጫ፣ በሐሳብ የተለየን ሰው ሞግቶ፣ በአመለካከት የተለየን በአመለካከት ረትቶ፣ ለአገር እና ለወገን የሚበጀውን ሐሳብ ማስፋት ሲቻል፣ ለዚያውም እንደ ግርማ የሺጥላ ዐይነቱን የሕዝብ እና የወገን አለኝታ ምሁር፣ በእንዲህ ዓይነት መልኩ መግደል መሸነፍ ነው፤ ብሏል፡፡

ፓርቲው፥ ምልአተ ሕዝቡን ያሳተፈ ጠንካራ የፖለቲካ ትግል በማድረግ፣ ሕግ የማስከበር ርምጃዎችን በማጠናከር፣ ጽንፈኝነትን ለመግታት ከምንጊዜውም በበለጠ ጠንክሮ እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ “ነውጠኛ ጽንፈኞች” ያሏቸውን አካላት፣ ለግድያው ተጠያቂ አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአቶ ግርማን መገደል በአስታወቁበት የፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ፤ “ከእኛ የተለየ ሐሳብ ማሰብ አልነበረበትም ብለው የሚያምኑ ነውጠኛ ጽንፈኞች፣ የፈጸሙት አስነዋሪ እና አሠቃቂ ተግባር ነው፤” ሲሉ ድርጊቱን በአጽንዖት ኮንነዋል።

አያይዘውም፣ “ጽንፈኝነትን በጊዜ ታግለን ካላስወገድነው ወደ መጨራረስ እንደሚወስደን ጉልሕ ማሳያ ነው፤” ብለዋል።

በሕግ እና በሥርዐት እንጂ በደቦ ፍርድ የግልም ኾነ የቡድን፣ የሕዝብንም ሆነ የአገር ጥቅምና ፍላጎት ማሳካት እንደማይቻል የገለጹት፣ የዐማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፍአለ በበኩላቸው፣ ሥርዐት አልበኝነትንና ሕገ ወጥነትን፣ ከመንግሥት ጎን ቆሞ እንዲያወግዝና እንዲታገል ለሕዝቡ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ዐብን በአወጣው መግለጫ፣ ድርጊቱ አግባብነት ባላቸው ተቋማት ሳይጣራና አጥቂዎቹ ተለይተው ሳይታወቁ፣ ከጥቃቱ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት ሲባል በአደባባይ እየተደረጉ ናቸው ያላቸውን ፍረጃዎች እና መግለጫዎች በጽኑ እንደሚያወግዝ አስታውቋል፡፡

መንግስታዊ አካላት ግድያውን የፈጸሙት ታጣቂዎች፣ ጽንፈኞችና ኢመደበኛ አደረጃጀት ያላቸው በማለት ቢጠቅሱም እስካሁን ከግድያው ጋር ተያይዞ ኃላፊነት የወሰደ አካል ግን የለም፡፡

ግድያው ተፈጸመ የተባለበት የመንዝ ጌራ ምድር ወረዳ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት፣ ስለ ጉዳዩ ዛሬ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ መግለጫ እንደሚሰጥ ቢያሳውቀንም፣ በተባለው ሰዓት ስንደውል ስልካቸው ሊመልስ አልቻለም፡፡

አቶ አቶ ግርማ የሺጥላ ማናቸው?

አቶ ግርማ የሺጥላ የዛሬ ሁለት ዓመት የአማራ ክልል የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ቢሮ ሓላፊ እጩ ኾነው ሲቀርቡ ለክልሉ ምክር ቤት በተነበበው የሕይወት ታሪካቸው መሰረት፤ የትውልድ ቦታቸው ሰሜን ሸዋ ዞን መሐል ሜዳ ሲኾን 48 ዓመታቸውን ነው።

የወቅቱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አገኘሁ ተሻገር አቶ ግርማ የሸጥላን ለክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሓላፊነት ለክልል ም/ቤት በእጩነት ሲያቀርቡ ባሰሙት አጭር የህይወት ታሪካቸው ከ1988 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት በሰሜን ሸዋ ዞን የአንጾኪያ ገምዛ የወረዳ ሥራ አስፈጻሚና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ ፤ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን አደረጀጃት ዘርፍ ኃላፊ፣ የደብረ ብርሃን ከተማ ምክትል ከንቲባ ኾነው አገልግለዋል።

የማስታወቂያ ወጣት ስፖርት ባህል ቱሪዝም ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የደብረ ብርሃን ፓርቲ ጉዳይ ኃላፊ፣ የባሶና ወረና ወረዳ አስተዳደር ማስታወቂያ ጸ/ቤት ኃላፊ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትልና ዋና አስተዳዳሪ ኾነው መሥራታቸውም ተገልጾ ነበር።

ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማእረግ የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በትምህርት ደረጃቸው በቢዝነስ አድሚነስትሬሽን ሁለተኛ ድግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡

በተወለዱ በ48 ዓመታቸው ህይወታቸው ያለፈው አቶ ግርማ የሽጥላ ወልደ ጻዲቅ ባለትዳርና የልጆች አባት መሆናቸው ታውቋል፡፡

አቶ ግርማ ከመገደላቸው አንድ ቀን አስቀድሞ፤ በሰሜን ሸዋ ዞን በደብረ ብርሃን ከተማ የሥራ ጉብኝት ማካሄዳቸው ተገልጾ ነበር።

የአቶ ግርማ የሽጥላ የአስከሬን ሽኝት እሁድ አዲስ አበባ ላይ እንደሚደረግ ፓርቲው የቀብር አስፈጻሚውን ኮሚቴ ጠቅሶ ይፋ አድርጓል። ቀብራቸውም በወላጆቻቸው ጥያቄና ፍላጎት መሰረት በትውልድ አገራቸው ስሜን ሸዋ ዞን መሃል ሜዳ ይፈጸማል ብሏል።

XS
SM
MD
LG