በዐማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ ከክልሉ ዐቅም በላይ እንደኾነ በመገለጹ፣ ላለፉት ዐሥር ወራት ተደንግጎ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ የሕግ ተፈጻሚነት፣ ባለፈው ግንቦት 24 ቀን ቢገባደድም፣ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ትጥቃዊ ግጭቶች መቀጠላቸውን፣ ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው በደቡብ ጎንደር እንዲሁም በሰሜን፣ ምዕራብ እና ምሥራቅ ጎጃም ዞኖች የሚገኙ ነዋሪዎች፣ ዐዋጁን መሠረት አድርገው የተላለፉ ክልከላዎች አሁንም እንዳሉ በመኾናቸው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተባብሰዋል፤ ብለዋል።
ከክልሉ ተመርጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የኾኑት አቶ አበባው ደሳለው፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ማብቃቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን እንደሚቀንስ ቢጠብቁም፣ በተፃራሪው እየከፋ መምጣቱ እንዳሳዘናቸው አመልክተዋል።
የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በኾነ መንገድ መከናወን እንዳለበት ያስገነዘቡ አንድ የሕግ ባለሞያ በበኩላቸው፥ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 መሠረት፣ የሥራ ጊዜው ያበቃውን የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ቀሪ ማድረጉን ወይም ማራዘሙን፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በግልጽ አቅርቦ ማሳወቅ ወይም ማጸደቅ እንደነበረበት ተናግረዋል።
ከአማራ ክልል እና ከፌደራል መንግሥት ምላሽ አላገኘንም።