ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት/ኔቶ/ አባል ሀገራት፣ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ባይደን ጥያቄውን ያቀረቡት፣ በሐምሌ ወር ከሚካሔደው ጉባኤ ቀደም ብሎ፣ ትላንት ማክሰኞ፣ ከጦር ቃል ኪዳን ጥምረት ሓላፊ ጋራ በተነጋገሩበት ወቅት ነው። ለሐምሌ የተቀጠረው ጉባኤ በአመዛኙ፣ በዩክሬን ግጭት እና 31 አባላትን ያቀፈው ኅብረት ዋና ሓላፊ የንስ ስቶልትንበርግ በዚኹ ዓመት ከሥልጣናቸው ሲለቁ በሚተኳቸው ሰው ላይ ያተኩራል፤ ተብሎ ይጠበቃል።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ ከስቶልትንበርግ ጋራ በነበራቸው ቆይታ፣ ዩክሬንን ከሩሲያ ጥቃት ለመከላከል ቁርጠኝነት እንዳላቸው አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። በሐምሌ ወር፣ በሊትዌኒያ ዋና ከተማ ከሚካሔደው የኔቶ ዓመታዊ ጉባኤ ቀደም ብለውም፣ ለወታደራዊ ርዳታ የሚውል ተጨማሪ 325 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር፣ ለዩክሬን እንደሚለግሱ ቃል ገብተዋል።
ባይደን፥ ኔቶ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ቢያወድሱም፣ 31ዱ አባል ሀገራት፣ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት እድገታቸው(GDP) ቢያንስ ሁለት በመቶ የሚኾነውን፣ ለመከላከያ ተግባር ለማዋል የገቡትን ቃል እንዲተገብሩ አሳስበዋል።
“የኔቶን ምሥራቃዊ ጎን አጠናክረናል፡፡ በኔቶ አባል ሀገራት ግዛት ሥር የሚገኘውን እያንዳንዱን ሥፍራ እንደምንጠብቅም ግልጽ አድርገናል። አሁንም እደግመዋለኹ፤ ዩናይትድ ስቴትስ፥ ለኔቶ ሕግ አንቀጽ አምስት ያለው ቁርጠኝነት፣ የአድማስ ደንጊያን ያክል የጠነከረ ነው፤” ያሉት ባይደን፣ የቀጣዩ ወር የሊትዌኒያ ጉባኤ፣ በዚኽ መንፈስ እንደሚካሔድና አባል ሀገራት፣ ሁለት ከመቶ የኾነ በቂ ወጪ ለመከላከያ እንደሚያወጡ የማረጋገጥ ሥራ እንደሚሠራ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
በዚኽ ዓመት መጨረሻ ሥልጣናቸውን የሚለቁት ስቶልትንበርግ በበኩላቸው፣ የሐምሌ ወሩ ጉባኤ፥ ኔቶ ለዩክሬን የሚሰጠውንና የሩሲያን ወረራ በመግታት በቅርቡ መልሶ ማጥቃት ለመጀመር ያስቻለውን ድጋፍ እንደምን ማጠናከር ይቻላል፤ በሚለው ላይ ያተኩራል፤ ብለዋል።
“ለዩክሬን በጋራ እየሰጠነው ያለነው ድጋፍ፣ አሁን እየተነጋገርን ባለንበት ወቅት፣ ጦርነቱ በሚካሔድበት ቦታ ላይ ለውጥ እያመጣ ነው። ምክንያቱም፣ መልሶ ማጥቃቱ ተጀምሯል፤ ዩክሬናውያን ለውጥ እያመጡ ነው። በርግጥ ገና ጅምር ላይ ነው፡፡ ኾኖም ዩክሬናውያን፣ ተጨማሪ መሬት ነፃ ማውጣት በቻሉ ቁጥር፣ በድርድር ጠረጴዛው ላይ ጠንካራ እጅ እንዲኖራቸው እንደሚያስችል እናውቃለን፤” ነው ያሉት ስቶልትንበርግ።
ዩክሬን፣ እጅግ አብዝታ የምትሻው የመከላከያ ጥምረቱ ድጋፍ ግና፣ አንድ ነገር ነው። የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮለድሚር ዘለንስኪ፣ “እጅግ በጣም አስፈላጊ የኾነው ነገር፣ እኛ በአውሮፓ ኅብረት የሚኖረን ቦታ ነው፤ ብዬ አስባለኹ፤” በማለት ከዚኽ ቀደም እንደተናገሩት፣ ዩክሬን፥ ኔቶን ለመቀላቀል ያላትን ዝግጁነት ዳግም አጽንተዋል።
ጉዳዩን በቅርቡ የሚከታተሉ ተንታኞች ግን፣ ዩክሬን ኔቶን የመቀላቀሏ ነገር፣ “የማይኾን ነው፤” ይላሉ። በካቶሊክ ዩኒቨርስቲ መምህር እና በስልታዊ እና ዓለም አቀፍ ጥናቶች ማዕከል ጥናት አጥኚው ሚካኤል ኪማዥ፣ “ጉዳዩ ተዘግቷል ማለት አይደለም። ለዩክሬን ጠንካራ ድጋፍ እንዲደረግና ምናልባትም ወደፊት ኔቶን እንድትቀላቀል ትልቅ ጉጉት አለ። ነገር ግን፣ ይህ ተጨባጭ ተስፋ ከመኾኑ በፊት፣ አሁንም መፈተሽ ያለባቸው ብዙ ሣጥኖች አሉ፤” ይላሉ።
ዋና ጸሐፊው ስቶልትንበርግ፣ በዋሽንግተን እየተዘዋወሩ ከሌሎች የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋራም ተገናኝተዋል። ከዩናይትድ ስቴትስ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የሪፐብሊካኖች መሪ ሚች ማኮኔል ጋራ በነበራቸው ቆይታ፣ የኔቶ አባል ያልኾኑ እንደ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ያሉ ሀገራት፣ በሊትዌኒያው የሐምሌ ወር ጉባኤ ላይ እንዲገኙ መጋበዛቸውን እንደነገሯቸው ገልጸዋል። ማኮኔል አክለውም፣ በጉባኤው፣ ስዊድን በይፋ የኔቶን ጥምረት ትቀላቀላለች፤ ብለው እንደሚጠብቁም ስቶልትንበርግ አመልክተዋል።
የስዊድን ኔቶን የመቀላቀል ሒደት የዘገየው፣ ከአባል ሀገራት አንዷ የኾነችው ቱርክ፥ ስቶኮልም፣ አንካራ እንደ ጽንፈኛ የምትመለከተውን የፖለቲካ ፓርቲ ቅርንጫፍ ለማስወገድ፣ የሚጠበቅባትን አላደረገችም፤ በሚል ክሥ፣ ኔቶን እንዳትቀላቀል በመቃወሟ ነው። ኪማዥ እንደሚሉት ግን፣ የቱርክ ፍላጎት ከዚያም ያለፈ ነው።
“ስዊድን፣ የኔቶን ጥምረት መቀላቀል ስለምትፈልግ፣ ቱርክ ስዊድንን ተጠያቂ የምታደርግበት ዕድል ይፈጥርላታል። ነገር ግን ቱርክ፥ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ምናልባትም ከሌሎች የኔቶ አባላት ስምምነት በማግኘት፣ የስዊድንን አባልነት እንድታጸድቅ ያደርጓት ዘንድ ጨዋታ የያዘች ይመስለኛል፤” የሚሉት ኪማዥ፣ “ስለዚኽ፣ ጥቂት በቅንነት የቀረበ ጉዳይ ቢኖርም፣ በተወሰነ መልኩ አንካራ፣ በአንዳንድ ጉዳዮች የበላይነት ለማግኘት፣ እንደ ዘዴ እየተጠቀመችበት ነው፤” ሲሉ፣ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ኔቶን በቅርብ የሚከታተሉ ተንታኞች፣ የጥምረቱ ኅብረት ቁርጠኝነት፥ ዐዲስ በሚመረጠው መሪ ላይ እንደሚንጠለጠል ይናገራሉ። ኾኖም፣ ዋሽንግተንም ኾነች ተሰናባቹ የመከላከያው ጥምረት ዋና ጸሐፊ ስቶልትንበርግ፣ በጉዳዩ ላይ ዝምታን መርጠዋል።
ዘገባው የአኒታ ፓዎል ነው፡፡