በትግራይ ክልል ውስጥ ከሚገኙ አህጉረ ስብከት ጋራ ተቋርጦ የነበረውን መዋቅራዊ ግንኙነት ለማስቀጠል የተጀመረው ጥረት እንዲቀጥል፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ወሰነ፡፡
በትግራይ ክልል የሚገኙ የአራት አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት እና የአብያተ ክህነት አመራሮች የመሠረቱት “መንበረ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን” የተባለ ክልላዊ “ጠቅላይ ቤተ ክህነት”፣ በቅርቡ 10 ኤጲስ ቆጶሳትን እንደሚሾም በትላንትናው ዕለት ገልጾ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ላለፉት 16 ቀናት ሲያካሒድ የቆየውን የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ፣ ዛሬ ከቀትር በኋላ በሰጠው መግለጫ፣ ከትግራይ ክልል ለተሰማው የሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት ውሳኔ፣ ቀጥተኛ ምላሽ ባይሰጥም፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ተሠይሞ በሥራ ላይ የሚገኘው በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ ልዑክ፣ ከትግራይ ክልል አህጉረ ስብከት ጋራ ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት ለማስቀጠል የጀመረውን እንቅስቃሴ እንዲቀጥል መመሪያ መስጠቱን አስታውቋል፡፡
ለዚኽም፣ የተሠየመው ልዑክ፣ የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት በማነጋገር ተልዕኮውን እንዲፈጽም፣ ምልዓተ ጉባኤው መወሰኑን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አባ ማትያስ ቀዳማዊ፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ አዳራሽ በንባብ ያሰሙት መግለጫ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ካለፈው ግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ሲያካሒድ በቆየው የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባው ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በተመለከተ፣ ዛሬ ተሲዓት በኋላ በቅዱስ ሲኖዶስ አዳራሽ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ከውሳኔዎቹ መካከል፣ በመላው ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ የሰላም ኮሚቴ መሠየም እንደሚገኝበት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አባ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ለብዙኃን መገናኛዎች በንባብ መግለጫ ያመለክታል፡፡
የትግራይ ክልል አህጉረ ስብከት፣ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋራ በተያያዘ፣ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጋራ ተቋርጦ የቆየውን መንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ አንድነትን ለማስቀጠል የተጀመረው ጥረት እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶሱ ወስኗል፡፡
የክልሉ አህጉረ ስብከት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና የአህጉረ ስብከቱ ጽ/ቤቶች አመራሮች፣ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በመነጠል፣ አቋቋምነው ያሉት “መንበረ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ቤተ ክህነት” አሁንም በተናጠል ሥራውን እንደሚቀጥል፣ ትላንት ማክሰኞ፣ ግንቦት 15 ቀን በመቐለ በሰጡት መግለጫ አስታውቀው ነበር፡፡
በክልሉ “የመንበረ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ቤተ ክህነት”፣ በቅርቡ የ10 ኤጲስ ቆጳሳት ሹመት እንዲካሔድ ውሳኔ ስለማስተላለፉም፣ በትላንቱ መግለጫ ላይ ተመልክቷል፡፡
የሰሜን ምዕራብ ትግራይ - ሽረ እንዳሥላሴ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በሰጡት ማብራርያ፣ አምስት ኤጲስ ቆጶሳትን ለአገር ውስጥ፣ ሌሎች አምስት ኤጲስ ቆጶሳት ደግሞ ለውጭ ሀገራት አገልግሎት እንዲሾሙ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በበኩሉ፣ ዛሬ በሰጠው መግለጫው፣ ራሱን “መንበረ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን” ብሎ ከሚጠራው ክልላዊ ቤተ ክህነት ለተሰማው “የሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት ውሳኔ” ቀጥተኛ ምላሽ ባይሰጥም፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ተሠይሞ በሥራ ላይ የሚገኝ፣ አምስት አባላት ያሉት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ ልዑክ፣ ከትግራይ ክልል አህጉረ ስብከት ጋራ ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት ለማስቀጠል የጀመረውን እንቅስቃሴ እንዲቀጥል መመሪያ መስጠቱን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከትግራይ ክልል አህጉረ ስብከት ጋራ ተቋርጦ የነበረው ግንኙነት እንዲቀጥል በመሥራት ላይ መኾኑን፣ ከዚህ ቀደምም መግለጹ ይታወሳል፡፡ ይህ የመቀራረብ እና የእርቅ ሒደት ስለ ደረሰበት ደረጃ፣ በትላንቱ የመቐለ መግለጫ ላይ የተጠየቁት ሰሜን ምዕራብ ዞን - ሽረ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፣ “ስለ ኹኔታው የማውቀው ነገር የለኝም፤” ማለታቸውን፣ መግለጫን የተከታተለው የአሜሪካ ድምፅ የመቐለ ዘጋቢ ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ መሰል የመዋቅራዊ መከፋፈል አደጋ ያጋጠማት ከትግራይ ክልል አህጉረ ስብከት ጋራ ብቻ አይደለም፡፡ በኦሮሚያ ክልልም መሰል ልዩነቶች ተፈጥረው፣ በሦስት የቤተ ክርስቲያኒቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መሪነት፣ “የኦሮሚያ እና የብሔር ብሔረሰቦች ሲኖዶስ” የተባለ ተነጣይ ሲኖዶስ ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ሦስቱ አባቶች፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተቀባይነት ያላገኙ፣ 26 ኤጲስ ቆጶሳትን ሾመው እንደነበርና በዚኽም ሳቢያ በአገር አቀፍ ደረጃ አይሎ የነበረው ውጥረት በውይይት መፈታቱ ይታወሳል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አህጉረ ስብከት ተፈጥሮ በነበረው ወቅታዊ ችግር ምክንያት፣ በአህጉረ ስብከት መንበረ ጵጵስናዎች፣ አብያተ ቤተ ክህነት እና በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት መቋረጡን፣ በዛሬው መግለጫው ያነሣው ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ በርካታ ምእመናንና ካህናት ፣ በእስር እና በእንግልት ላይ እንደሚገኙም ገልጿል፡፡
እነዚኽ ችግሮች እንዲቀረፉና መደበኛው የአሠራር መዋቅራዊ አንድነት እንዲመለስ፣ ሰባት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን በመሠየም፣ ከፌዴራል እና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋራ በመወያየት፣ ችግሮች እንዲፈቱ እንዲደረግ መወሰኑንም አስታውቋል፡፡
በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች፣ በተደራቢነት በተያዙ እና ችግር ባለባቸው አህጉረ ስብከትም፣ ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ በመወሰን፣ ተሿሚዎቹን ዕጩ መነኰሳት ከቋሚ ሲኖዶስ ጋራ በመተባበር፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ለይቶ የሚያዘጋጅ ሰባት አባላት ያሉት የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙም ተመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ በወቅታዊ ችግር ምክንያት በመላው አገሪቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በአጠቃላይ፣ ችግሮቻቸውን በጥናት በመለየት፣ ኹለንተናዊ ሰብአዊ ድጋፍ፣ የማጽናናት እና የመጎብኘት መርሐ ግብሮች እንዲደረጉ ያዘዘው ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ በትግራይ ክልል ያለውን ከፍተኛ ችግር ታሳቢ በማድረግ፣ የኻያ ሚሊዮን ብር አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ ማድረጉን አመልክቷል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱን የመጪ ዐሥር ዓመታት የመንፈሳዊ እና ዘላቂ ልማት ግብ መሪ ዕቅድ በምልዓተ ጉባኤው ማጽደቁን የጠቀሰው ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ በኹሉም መዋቅሮች ተግባራዊ እንዲደረግም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
በኢሉ አባቦራ መቱ ሀገረ ስብከት መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲከፈት እና በሌሎችም አህጉረ ስብከት ሊከፈቱ የታሰቡ ኮሌጆችን በተመለከተ ደግሞ ጥናት እንዲደረግ መመሪያ መስጠቱንም ቅዱስ ሲኖዶሱ በመግለጫው አስታውቋል፡፡