በኦሮምያ ክልል የረሃብ አደጋ መጋረጡን በማስጠንቀቅ ሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ እንዲቻል ጊዜያዊ የተኩስ ማቆም እንዲደረግ ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የሚመለውና መንግሥት በአሸባሪነት ፈርጆ ሸኔ እያለ የሚጠራው አማፂ ቡድን መጠየቁን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።
ትናንት በቃል አቀባዩ ኦዳ ተርቢ የወጣው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መግለጫን ጠቅሶ የዜና ወኪሉ እንዳስነበው፤ በድርቅ ለተጠቁ አካባቢዎች ሰብዓዊ ድርጅቶች ዕርዳታ ማድረስ እንዲችሉ፣ ተኩስ የማቆም ትብብር የማድረግ ሐሳብ አቅርቧል።
“የተኩስ ማቆሙ ሐሳብ ተቀባይነት ካላገኘ ወይም የኢትዮጵያ መንግሥት በሥምምነቱ ላይ ለመነጋገር በሚያመነታበት ግዜ ሰብዓዊ መተላለፊያ እንከፍታለን” ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ለማድረግ ተሞክሮ ወዲያው ሊገኙለት እንዳልቻለ የዜና ወኪሉ በዘገባው አመልክቷል።