በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአሜሪካ የተደገፈው የኢትዮጵያ የፍትሕ ማሻሻያ ፕሮጀክት የተቋማቱን ዐቅም መለወጡ ተገለጸ


በአሜሪካ የተደገፈው የኢትዮጵያ የፍትሕ ማሻሻያ ፕሮጀክት የተቋማቱን ዐቅም መለወጡ ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:04 0:00

- “አስተዋፅኦ ቢኖረውም የተቋማቱን ነፃነት እና ገለልተኝነት ግን አያረጋግጥም”-እንባ ጠባቂ ተቋም

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት ወይም ዩኤስ-ኤይድ፣ ባለፉት አራት ዓመታት፣ በኢትዮጵያ የተተገበረው የፍትሕ ሥርዐት ማሻሻያ ፕሮጀክት፣ በፍትሕ ተቋማት ላይ፣ የዐቅም ግንባታ ለውጥ እንዳስገኘ ተገለጸ፡፡

የፕሮጀክቱን ፍጻሜ ለመገምገም፣ በዐዲስ አበባ በተዘጋጀ ሥነ ሥርዐት ላይ የተሳተፉ ባለሥልጣናት እና የልዩ ልዩ ተቋማት ተወካዮች፣ የፌዴራሉን እንዲሁም የዐማራ እና የኦሮሚያ ክልሎችን የፍትሕ ተቋማት በትግበራው ያካተተው ፕሮጀክቱ፥ የፍትሕ እና የዴሞክራሲ ተቋማትን ዐቅም በመገንባት ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ይህም ተቋማቱን፣ ከፖለቲካ ተጽእኖ ለማላቀቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው፣ የፕሮጀክቱ ምክትል ሓላፊ አቶ ማንደፍሮ በላይ አመልክተዋል፡፡

በሥነ ሥርዐቱ ላይ የተናገሩት የዩኤስኤይድ የኢትዮጵያ ተልዕኮ ምክትል ሓላፊ ቶም ስታል፣ የአሜሪካ መንግሥት፣ በኢትዮጵያ የሚካሔደውን የፍትሕ ሥርዐት ማሻሻያ ለማገዝ ቁርጠኛ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ዶር. እንዳለ ኃይሌ በበኩላቸው፣ ድጋፉ፥ ተቋማቱን ከመንግሥት ተጽእኖ ለመጠበቅ የራሱ አስተዋፅኦ ቢኖረውም፣ የተቋማቱ ነፃነት እና ገለልተኝነት ግን በዚኽ እንደማይረጋገጥ፣ በዝግጅቱ ላይ ተናግረዋል፡፡

ከአራት ዓመታት በፊት፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት በቀረበ ጥያቄ ላይ ተመሥርቶ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በ1ነጥብ2 ቢሊዮን ብር ሲተገበር የቆየው፣ የዩኤስ-ኤይድ የፍትሕ ማሻሻያ ፕሮጀክት፥ በሰው ኃይል

ሥልጠና፣ በተቋማት ዐቅም ግንባታ፣ በሕጎች እና መመሪያዎች ቀረፃ፣ በመሣሪያዎች ድጋፍ እና በግንዛቤ ማሳደጊያ ተግባራት ላይ ትኩረት ያደረገ እንደነበር ተገልጿል፡፡

የፕሮጀክቱ ትግበራ፣ ከፌደራል ተቋማት አልፎ፣ የኦሮሚያንና የዐማራ ክልሎችን እንዳካተተ የተገለጸ ሲኾን፣ በሁለቱም ክልሎች ባሉት የፍትሕ ተቋማት አሠራር ላይ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል፤ ተብሏል፡፡

አቶ አብዬ ካሳሁን፣ የዐማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት፡፡

ከኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የመጡት አቶ ሑሴንም፣ ፕሮጀክቱ ጠቀሜታ አለው ብለው ያምናሉ፡፡

በፕሮጀክቱ የተከናወኑት የዐቅም ግንባታ ሥራዎች፣ የፍትሕ እና የዴሞክራሲ ተቋማቱን፣ ከፖለቲካ ተጽእኖ ለማላቀቅ አስተዋፅኦ እንዳላቸው፣ የፕሮጀክቱ ምክትል ሓላፊ አቶ ማንደፍሮ በላይ አመልክተዋል።

ይህም ኾኖ፣ በፍትሕ ሥርዐቱ መጥቷል የሚባለው የዐቅም ግንባታ ለውጥ፣ በበቂ ኹኔታ ውጤቱ ጎልቶ አለመታየቱን፣ የሚናገሩ አስተያየት ሰጪዎች፣ ዳኞች ካለባቸው የደኅንነት ስጋት ሳቢያ በከፍተኛ ቁጥር ሥራቸውን መልቀቃቸው፣ የአስፈጻሚው አካል ትብብር ማነስ እና የሚከፈላቸው ደመወዝ ከሥራ ጫና አኳያ አለመመጣጠን፣ የፍትሕ ሥርዐቱን ነፃነት እና ገለልተኝነት እየጎዳው ስለመኾኑ፣ ቀደም ሲል መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ከዚኹ ጋራ በተያያዘ፣ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ዶር. እንዳለ ኃይሌ በበኩላቸው፣ እንዲህ ዐይነት ድጋፍ፥ የፍትሕ ተቋማትን ከመንግሥት ተጽእኖ ለማላቀቅ አስተዋፅኦ ቢኖረውም፣ የተቋማቱ ነፃነት እና ገለልተኝነት ግን በዚኽ አይረጋገጥም፤ ይላሉ፡፡

የዩኤስኤይድ የኢትዮጵያ ተልዕኮ ምክትል ሓላፊ ቶም ስታል በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ፥ የተለያዩ ለውጦችን ማስመዝገቡን ተናግረው፣ ወደፊትም የአሜሪካ መንግሥት፣ የፍትሕ ሥርዐት ማሻሻያ እንቅስቃሴዎችን ለማገዝ ቁርጠኛ እንደኾነ አረጋግጠዋል፡፡

“ዩኤስ-ኤይድ እና የአሜሪካ መንግሥት፣ በኢትዮጵያ የፍትሕ ተደራሽነትን ለማስፋት፣ የፍትሕ ሥርዐቱን ለማሻሻል፣ እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ጥበቃን ለማበረታታት የሚደረጉ ጥረቶችን ለመደገፍ፣ ቁርጠኞች ናቸው፡፡ ይህ፣ በኢትዮጵያ የሚተገበረውን የሽግግር ፍትሕንም ያካትታል፡፡ በመላ አገሪቱ ሰው ተኮር

የፍትሕ ሥርዐት እንዲጎለብት፣ ጠንካራ ግንኙነት በመመሥረት ውጤታማ ትብብር ማድረጋችንን እንቀጥለን፡፡” የፍትሕ ሥርዐት ማሻሻያ ፕሮጀክቱ፣ የኢትዮጵያ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ የመሳሰሉትን የዴሞክራሲ ተቋማትን፣ እንዲሁም የሲቨል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትንና የብዙኃን መገናኛዎችንም፣ በተለያዩ የዐቅም ግንባታ ሥራዎች እንደ ደገፏቸው፣ በውይይቱ ላይ ተመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG