በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኦብነግ ሦስት አባላቱ ድንገት ተኩስ በከፈተ የመከላከያ አባል እንደተገደሉበት ገለጸ


ኦብነግ ሦስት አባላቱ ድንገት ተኩስ በከፈተ የመከላከያ አባል እንደተገደሉበት ገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:20 0:00

በትላንትናው ዕለት፣ በቀብሪደኀር ከተማ፣ አንድ የመከላከያ ሠራዊት አባል፣ ድንገት በከፈተው ተኩስ፣ አራት ሰዎችን ገድሎ፣ ሦስት ሰዎችን ማቁሰሉን፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር(ኦብነግ) አስታውቋል።

በተኩሱ የተገደሉት ሦስቱ ግለሰቦች፣ “አባሎቼ ናቸው፤” ያለው ኦብነግ፣ የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥት፣ ድርጊቱን በፍጥነት አጣርተው ርምጃ እንዲወስዱ ጠይቋል።

ባለፉት ስድስት ወራት፣ ወደ ክልሉ በተመለሱ አንዳንድ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ ልዩ ልዩ ጥቃቶች እየተፈጸሙ እንደሆነ ያወሳው ግንባሩ፣ የሠራዊቱ ካምፖች ከከተሞች እንዲርቁና የመከላከያ አባላት፣ ትጥቅ ይዘው ወደ ከተማ ከመግባት እንዲከለከሉ ጠይቋል።

የክልሉ ኮምዩኒኬሽንስ ቢሮ በበኩሉ፣ ድርጊቱን የፈጸመው ወታደር፥ ከካምፕ አምልጦ የጠፋና ለሦስት ቀናት ክትትል ሲደረግበት የቆየ እንደሆነ ገልጾ፣ አስቀድሞ ተኩሶ የመታውም፣ ተከታትለው የደረሱበትን የቀብሪ ደኀር ነዋሪ እና የከተማዋን አመራር አባል ነው፤ ብሏል።

ግድያውን የፈጸመው ወታደር፣ ተጨማሪ ጉዳት ከማድረሱ በፊት፣ በመከላከያ ሠራዊት አባላት ርምጃ እንደተወሰደበት ለከተማዋ ነዋሪዎች ተገልጿል።

የመከላከያ ሠራዊት አባሉ፣ በቀብሪ ደኀር ከተማ 08 ቀበሌ፣ ድንገት በከፈተው ተኩስ፣ ሦስት የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር አባላት እና አንድ የብልጽግና አመራር መገደላቸውን፣ እንዲሁም ሌሎች ሦስት ሰዎች መቁሰላቸውን፣ ግንባሩ በትዊተር ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የኦብነግ ቃል አቀባይ አቶ አብዱቃድር ሐሰን ሂርሞጌ፣ ባለፉት ስድስት ወራት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት አካባቢውን ለቆ የነበረው መከላከያ ሠራዊት ፣ ወደ ሶማሌ ክልል ከተመለሰ በኋላ፣ ይህን መሰል ጥቃት በልዩ ልዩ ከተሞች እየተሰማ እንደሆነ፣ ቃል አቀባዩ አውስተዋል።

ስለ ጉዳዩ መረጃ የሰጡን፣ የሶማሌ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ቢሮ ሓላፊ አቶ አብዱቃድር ረሺድ፣ በቀብሪደኀር ከተማ ግድያውን የፈጸመው ወታደር፣ ከሦስት ቀናት በፊት፣ ከመከላከያ ካምፕ ያመለጠና ክትትል እየተደረገበት የነበረ የመከላከያ ሠራዊት አባል ነው፤ ብለዋል።

ግድያውም፣ መከላከያን በካደ አንድ ግለሰብ የተፈጸመ እንጂ፣ በሠራዊቱ ደረጃ የተፈጸመ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

የኦብነግ ቃል አቀባይ አቶ አብዱቃድር ሐሰን ሂርሞጌ በበኩላቸው፣ የሶማሌ ክልል ሕዝብ፣ በዘመነ ኢሕአዴግ፣ በርካታ ጅምላ ጭፍጨፋዎች እንደተፈጸሙበት አስታወሰው፣ ዛሬም የመከላከያ ሠራዊቱን፣

እንደ ጠላቱ እንዲያይ ከሚያደርጉ አካሔዶች፣ መቆጠብ ተገቢ ነው፤ ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። ተመሳሳይ ጥቃቶች ዳግም እንዳይፈጸሙ፣ ርምጃዎች መወሰድ አለባቸው፤ ባይ ናቸው።

ከ1948 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በጎዴ፣ ቀብሪደኀር፣ ጂግጂጋ እና ሌሎችም አካባቢዎች የተቋቋሙ የመከላከያ ካምፖች፣ ከከተሞች ርቀው ድንበር አካባቢ መቋቋም እንደሚገባቸው አመልክተዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊት አባላቱም፣ በከተሞች ውስጥ የጦር መሣሪያ ይዘው እንዲንቀሳቀሱ ሊፈቀድላቸው አይገባም፤ ይላሉ።

በዛሬው ዕለት፣ የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች እና የሶማሌ ክልል አመራሮች፣ የቀብሪደኀር ከተማ ነዋሪዎችን ሰብስበው፣ ስለ ጉዳዩ እንዳወያዩዋቸው፣ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሓላፊ አቶ አብዱቃድር ረሺድ አስታውቀዋል።

XS
SM
MD
LG