በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩክሬን በሩሲያው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቀን በርካታ የድሮን ጥቃቶችን አደረሰች


 በቤልጎሮድ ላይ የበረረው ሰው አልባ አውሮፕላን እኤአ መጋቢት 14 ቀን 2024
በቤልጎሮድ ላይ የበረረው ሰው አልባ አውሮፕላን እኤአ መጋቢት 14 ቀን 2024

ዩክሬን የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን የሥልጣን ዘመን ለተጨማሪ ስድስት ዓመታት ለማራዘም በተዘጋጀው የመጨረሻው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እለት በርካታ የሰው አልባ አውሮፕላን (የድሮን) ጥቃቶችን በተለያዩ የሩሲያ ክልሎች አድርሳለች፡፡

የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር በሞስኮ ክልል የበረሩትን አምስቱን ጨምሮ፣ 35 የዩክሬን ድሮኖችን በአንድ ሌሊት መትቶ መጣሉን አስታውቋል።

ከሌሊቶቹ በተጨማሪ በዋና ከተማው ዶሞዴዶቮ አውሮፕላን ማረፊያ ዛሬ እሁድ ማለዳው ላይ አንድ ድሮን ተመትቶ መውደቁን የተናገሩት የሞስኮ ከንቲባ ሰርጌይ ሶቢያኒን፣ ድሮኖቹ በሞስኮ ምንም አይነት ጉዳት እና የንብረት ውድመት አላደረሱም ብለዋል፡፡

መጠነ ሰፊ ናቸው የተባሉት የዩክሬን የድሮን ጥቃቶች ከተፈጸሙባቸው ክልሎች መካከል ፣ የካሉጋ ክልል፣ ከሞስኮ ሰሜናዊ ምስራቅ ከዩክሬን ድንበር 800 ኪሎ ሜትር (500 ማይል) ርቀት ላይ የሚገኘው የያሮስቪል ክልል፣ የቤልጎሮድ፣ ኩርስክ እና ሮስቶቭ የተባሉ የሩሲያ ክልሎች እንደሚገኙበት የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የቤልጎሮድ ገዥ ቪያቼስላቭ ግላድኮቭ በዩክሬን ድሮን ጥቃት የ16 ዓመቷ ልጃገረድ ስትሞት ወላጅ አባቷ መቁሰላቸውን ተናግረዋል፡፡

በክራስኖዶር ክልል በሚገኝ የነዳጅ ማጣሪያ ላይ አንድ ሰው አልባ አውሮፕላን በመውደቁ የእሳት አደጋ መፈጠሩን እና አንድ ሰራተኛ መሞቱን ባለስልጣናት ተናግረዋል።

የነዳጅ ማጣሪያዎች እና የነዳጅ ማጠራቀሚያዎች የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖች ዋነኛ ኢላማዎች እንደነበሩ ተመልክቷል፡፡

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን ፣ ጥቃቶቹ የተካሄዱት ዩክሬን የሩሲያን ነዋሪዎች ለማስፈራራት እና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን ለማደናቀፍ ባለፉት ጥቂት ቀናት ያደረገቸው የድሮን ወረራዎች እና ሌሎች ጥቃቶችን ተከትሎ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ዓርብ ለሀገሪቱ የጸጥታ ምክር ቤት እንደተናገሩት “እነዚያ ጥቃቶች የአጸፋ ቅጣት ሳያገኙ አይቀሩም” ሲሉ ዝተዋል፡፡

በሌላም በኩል የዩክሬን ጦር 14 የሚደርሱ የሩሲያ ድሮኖች በኦዴሳ ክልል ዛሬ እሁድ ተመተው መውደቃቸውን አስታውቋል፡፡

ጥቃቱ የተፈጸመው ባላፈው ዓርብ የሩሲያ ባለስቲክ ሚሳዬሎች የወደቢቱን ደቡባዊ ከተማ በማጥቃት ቢያንስ 21 ሰዎችን ከገደሉና በርካታ ቤቶችን ካቃጠሉ በኋላ መሆኑን ባለሥልጣናት ተናግረዋል፡፡

ወደ ሶስተኛ ዓመቱ በተቃረበው ጦርነት የሩሲያ ኃይሎች አዝጋሚ በሆነ ሂደት አንዳንድ ይዞታዎችን በመያዝ ድሎችን ቢያስመዘግቡም የዩክሬን ኃይሎች ድንበር ተሻግረው ሩሲያው ውስጥ ዘልቆ በመግባት ተጨማሪ የድሮን ጥቃቶችን እየሰነዘሩ ነው፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG