በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በተላለፈው ሰላማዊ ሰልፍ የታሰሩ ፖለቲከኞችን ለማስለቀቅ “አካልን ነጻ የማውጣት” ክስ መመሥረቱ ተገለጸ


የኢትዮጵያ ካርታ
የኢትዮጵያ ካርታ

“አካልን ነጻ የማውጣት” ክሱ እንደተመሠረተ ያስታወቁት የኢሕአፓ ሊቀ መንበር ረዳት ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ፣ በእስር ላይ ከነበሩ አራት የሰልፉ አስተባባሪዎች ውስጥ አንዱ እንደተለቀቁም ገልጸዋል፡፡

ፖለቲከኞችን ጨምሮ ከሰላማዊ ሰልፉ ጋራ በተገናኘ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ኹሉም ታሳሪዎች እንዲለቀቁም፣ ፓርቲያቸው ባወጣው መግለጫ ጠይቋል፡፡

ከታሰሩ ሁለት አባላቱ ውስጥ አንዱ እንደተለቀቁ የገለጸው እናት ፓርቲ፣ በተሰረዘው ሰላማዊ ሰልፍ ምክንያት የተያዙ ታሳሪዎች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጠይቋል፡፡

ጉዳዩ ያሳስበናል ያሉት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ፣ ወቅታዊ የአገሪቱ ቀውሶች በውይይት መፈታት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

በዐዲስ አበባ ከተማ፣ ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ሊካሔድ ታቅዶ ላልተወሰነ ጊዜ ከተላለፈው ሰላማዊ ሰልፍ ጋራ በተገናኘ፣ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ የሰልፉ አስተባባሪዎች መካከል አንዱ እንደተለቀቁ፣ ሰልፉን ከጠሩ ፓርቲዎች ውስጥ አንዱ የኾነው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ(ኢሕአፓ) ሊቀ መንበር ረዳት ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ ተናግረዋል፡፡ የቀሩትም እንዲለቀቁ ደግሞ፣ የአስተባባሪው ኮሚቴ አባላት ክስ እንደመሠረቱ፣ ሊቀ መንበሩ ገልጸዋል፡፡

አስተባባሪዎች ከተባሉት ውስጥ አንዱ እና የትንሣኤ ሰባ እንደርታ ፓርቲ ጸሐፊ የኾኑት ካልኣዩ መሓሪ፣ በማይታወቅ ኹኔታ ከእስር መለቀዋቸውን የተናገሩት ሊቀመንበሩ፤ “የቀሩት ሦስቱ አስተባባሪዎቹ አኹንም በእስር ላይ ናቸው፡፡ እነርሱም፣ የኢሕአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር መጋቤ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት፣ የሰባ እንደርታ ምክትል ሊቀ መንበር ጊደና መድኅንና እንደተቆርቋሪ ግለሰብ አቶ ናትናኤል መኰንን(የቀድሞ የኢዜማ አመራር አባል) ናቸው፡፡ በሦስቱ ጉዳይ፣ አካልን ነጻ ማውጣት በሚለው የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዐት መሠረት፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮን በመደበኛ ፍርድ ቤት ከሰናል፡፡” ብለዋል።

እስረኞቹ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ ሲገባቸው ባለመቅረባቸው ክሱን መመስረታቸውን የገለፁት ረዳት ፕሮፌሰር ዝናቡ፤ ክሱን የመሰረቱት ፖሊስ እስረኞቹን ለምን ፍርድ ቤት እንዳላቀረበ እንዲጠየቅና በነጻ እንዲለቃቸው መኾኑን ተናግረዋል፡፡ “እነዚኽ ሰዎች በተጠረጠሩበት ቦታ ሊቆዩ ሲገባ፣ አዋሽ አርባ ወደሚባል ማጎሪያ ቦታ ወስደዋቸዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውን፣ ጠበቃ እና የመሳሰሉትን ማግኘት አልቻሉም፡፡ እኛም እስከ አኹን አላገኘናቸውም፡፡ በከፍተኛ ፍርድ ቤት 8 ችሎት ባቀረብነው ክስ እነኚኽን ነጥቦች አካተናል፡፡ ፖሊስ ነገ መልስ እንዲሰጥ ፍርድ ቤቱ አዟል፡፡ በመጪው ሰኞ ዕለት ውሳኔ ይሰጣል፡፡” ብለዋል።

ከፖለቲከኞቹ በተጨማሪ፣ በሰላማዊ ሰልፉ ምክንያት የታሰሩ ግለሰቦች ኹሉ፣ “በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ” የኢሕአፓ ሊቀ መንበር ረዳት ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ ጠይቀዋል፡፡

ከሰልፉ ጋራ በተገናኘ፣ በዐዲስ አበባ ከተማ ባሉ የተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ፣ “በርካታ ወጣቶች ታስረው እንደሚገኙ” መረጃው እንዳላቸው የገለጹት ሊቀ መንበሩ፣ “ታሳሪዎቹን በስማቸው ለይተን ብናውቅ፣ ለእነርሱም አካልን ነጻ የማውጣት ክስ እንመሰርት ነበር፤” ብለዋል፡፡

የጸጥታ እና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል፣ ባለፈው ሳምንት ኀሙስ፣ ኅዳር 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ “በሰላማዊ ሰልፍ ሽፋን በዐዲስ አበባ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ያቀዱ 97 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፤” ሲል ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ በቁጥጥር ሥር ስለዋሉት ተጠርጣሪዎች ማንነት ግን በይፋ አልገለጸም፡፡

የመንግሥት ርምጃ፣ “ኾን ተብሎ ሰልፉን ለማስቀረት የተደረገ ነው፤” ያሉት አስተባባሪዎቹ፣ ሰልፉን ለሌላ ጊዜ እንዳስተላለፉት መግለጻቸው ይታወቃል፡፡

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም፣ ከሰልፉ ጋራ በተገናኘ ሰዎች መታሰራቸውን በመቃወም መግለጫ ማውጣታቸው ይታወቃል፡፡ ከእነዚኽም አንዱ የኾነው እናት ፓርቲ፣ “በጅምላ የታሰሩ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ እንጠይቃለን፤” ብሏል፡፡

የእናት ፓርቲ ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ አቶ ዳዊት ብርሃኑ፣ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት አስተያየት፣ “ምንም እንኳን በሰላማዊ ሰልፉ ጥሪ ውስጥ ተሳትፎ ባይኖረንም፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ መብት እንደኾነ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ውስጥ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ በጸጥታው ጉዳይ መንግሥት ተባባሪ እንዲኾን እንጠብቃለን፡፡ ገና ለገና፣ ሰላማዊ ሰልፍ የሚያደርጉ አካላት ጥሪ አድርገዋል፤ በሚል ሰበብ፣ ከጉዳዩ ጋራ ምንም ግንኙነት የሌላቸው ወጣቶች እና የዐዲስ አበባ ነዋሪዎች ከየቦታው እየታፈሱ ኢ-ሰብአዊ በኾነ አያያዝ በየፖሊስ ጣቢያው እንደሚገኙ ለመረዳት ችለናል፡፡ እነዚኽ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንደጠይቃለን፡፡” ሲሉ የፓርቲያቸውን አቋም አንጸባርቀዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት የታሰሩት የፓርቲው የቀድሞ ጠቅላይ ጸሐፊ አቶ ጌትነት ወርቁ፣ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 2 ቀን እንደተለቀቁ የተናገሩት አቶ ዳዊት ብርሃኑ፣ የፓርቲው የሕግ እና ሥነ ሥርዐት ክፍል ሓላፊ አቶ ዋለልኝ አስፋው ግን፣ በእስር ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ስለ እስሩ ምክንያት ግን፣ ታሳሪዎቹ ከፖሊስ የተነገራቸው ምንም መረጃ እንደሌለ አመልክተዋል፡፡

ከሰላማዊ ሰልፉ ጋራ በተገናኘ እየተፈጸመ ያለው እስር ያሳስበናል ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ እና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲ አንድነት መድረክ ዋና ጸሐፊ አቶ ደስታ ዲንቃ፣ “ሰልፉን የጠሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ‘የሕዝብ ጥያቄ ይሰማ፤ ጦርነቶች ይቁሙ’ ነው የሚሉት፡፡ ጥያቄያቸው፣ ለመንግሥት ብቻ ሳይኾን፣ ጫካ ገብተው ከመንግሥት ጋራ ለሚታገሉትም ሊቀርብ ይችላል፡፡” ሲሉ ለሰልፉ ጥሪ እና ለእስሩ ምክንያት የኾኑ ወቅታዊ ችግሮች በውይይት ሊፈቱ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

አክለውም “በጦርነት ውስጥ ያሉትን ኹሉንም አካላት ይመለከታል፡፡ በመንግሥት በኩል ደግሞ፣ አኹን ካሉት ዘርፈ ብዙ ችግሮች እና ግጭቶች አንጻር፣ ሰላማዊ ሰልፉ ከተደረገ ሌላ ችግር ያስከትላል፤ ብሎ ሊሰጋ ይችላል፡፡ በአንጻሩ፣ ዜጎችን ሰላማዊ ሰልፍ መከልከል ሕጋዊ አይደለም፡፡ ለገጠመን ወቅታዊ ምስቅልቅል ትክክለኛው መፍትሔ፣ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ቁርጠኛ መኾን ነው፡፡” ብለዋል።

የጸጥታ እና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኀይሉ፣ በሽብር ጠርጥሬያቸዋለኹ ያላቸውን 97 ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንዳዋለ ከማስታወቅ ባለፈ፣ ተጠርጣሪዎቹን ለፍትሕ የማቅረብ ሒደቱ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣ የገለጸው ነገር የለም፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG