በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አሜሪካ የ106.5 ሚሊዮን ዶላር ታንክ ተተኳሾችን ለእስራኤል ለመሸጥ ወሰነች


ፎቶ ኤፒ (ታህሳስ 10፣2023)
ፎቶ ኤፒ (ታህሳስ 10፣2023)

የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ 14ሺሕ የሚሆኑ እና 106.5 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የታንክ ተተኳሾችን በአስቸኳይ ለእስራኤል እንዲሸጥ እንደወሰነ አስታውቋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንተኒ ብሊንከን፣ የአሜሪካ ብሔራዊ የደህንነት ሁኔታን በተመለከተ አስቸኳይ ሁኔታ በመኖሩ፣ ሽያጩ በአጣዳፊ እንዲከናወን መወሰናቸውን እና፣ መ/ቤቱም ውሳኔውን ለአሜሪካ ም/ቤት ዓርብ ምሽት እንዳሳወቀ ተነግሯል።

ለውጪ አገራት መሣሪያ ለመሸጥ የኮንግረስ ይሁንታ የሚያስፈልግ ቢሆንም፣ አስተዳደሩ አስቸኳይ ሁኔታ ተፈጥሯል በሚል ወቅት ግን፣ ካለ ኮንግረስ ፈቃድ ከዚህ በፊትም ተሽጦ እንደሚያውቅ የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በደቡብ ጋዛ ከባድ ውጊያ መቀጠሉ ተዘግቧል።

በሰሜን ጋዛ በነበረው ጦርነት ምክንያት ፍልስጤማውያን ወደ ደቡብ ጋዛ እንዲሄዱ ተነግሯቸው የነበረ ቢሆንም፣ ጦርነቱ ተከትሏቸው መጥቷል። የእስራኤል ጦር ጥቃቱን ወደ ደቡብ የጋዛ ሰርጥ እንደሚያስፋፋ አስታውቋል። እስከ አሁን 7ሺሕ የሚሆኑ የሐማስ ታጣቂዎችን እንደገደለች እስራኤል አስታውቃለች፡፡

በጋዛ የሚገኘው እና በሐማስ የሚተዳደረው የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ፣ በእስራኤል ጥቃት እስከ አሁን 18ሺሕ ሰዎች ሲገደሉ፣ በአብዛኛው ሕፃናት እና ሴቶች መሆናቸውን ያስታውቃል።

የዓለም ጤና ድርጅት የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ፣ በጋዛ ስላለው የጤና ሁኔታ ዛሬ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።

አሜሪካ በተመድ የፀጥታው ም/ቤት ሊወጣ የነበረውን የሰብዓዊ ትኩስ ማቆም የውሳኔ ሃሳብ፣ ድምጽን በድምጽ በመሻሯ፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ነታያሁ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG