በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ያለው ጦርነት፣ እስራኤል ከሳዑዲ አረቢያ እና ከሙስሊሙ ዓለም ጋራ መቀራረብ ለመፍጠር የምታደርግውን ጥረት ጥርጣሬ ውስጥ ከቶታል ሲሉ ተንታኞች በመናገር ላይ ናቸው። ግጭቱ በፓኪስታን ውስጥ የነበረውና ለእስራኤል እውቅና መስጠትን በተመለከተ የሚደረገውን ክርክርም እንዲረግብ አድርጎታል።
ኢስላማባድ፤ ከእስራኤል ጋር የዲፕሎማሲ ግኑኝነት የላትም። ፍልስጤም ሀገር ሆና እስከምትመሠረት ድረስ እስራኤልን እንደ ሉአላዊ አገር እንደማትቀበል አስታውቃለች፡፡ ይህም በአብዛኛው የእስልምና ተከታይ የሆኑ ሀገሮች የረጅም ጊዜ አቋም እንደሆነ ይታወቃል። ፓኪስታናውያን ሃይውዷን ሀገር መጎብኘት አይችሉም፣ ምክንያቱም ፓስፖርታቸው “ከእስራኤል በስተቀር ለሁሉም ሀገራት የሚያገለግል” የሚል ማሳሰቢያ ተጽፎበታል።
ሆኖም ግን፣ ፓኪስታን በእስራኤል ላይ ያላትን አቋም እንደገና መመርመር ይገባት እንደሁ፣ በዋና ዋና ቴሌቭዥን ቻነሎች፣ በጋዜጦች፣ እና በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች፣ ያዝ ለቀቀ እያለ የሚደረጉ ክርክሮች አሉ። ሁለቱ ሀገራት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው በእ.አ.አ 2005 ከተገናኙ ወዲህ፣ የጸጥታ ጉዳዮችን በተመለከተ በሚስጥር ስብሰባ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
አሁን በፓኪስታን በመደረግ ላይ ያለው ክርክር መነሻው ደግሞ፣ በአሜሪካ አሸማጋይነት በተፈጠረው “የአብረሃም ስምምነት” መሰረት በእስራኤል እና በሳዑዲ አረብያ መካከል ግንኙነት እንዲኖር የሚያስችል ጥረት በመኖሩ እንዲሁም፣ በዚሁ ስምምነት መሠረት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ባህሬን ከሶስት ዓመታት በፊት ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማሻሻላቸው ምክንያት ነው።
ፊሼል ቤንክሃልድ የተባለ ፓኪስታናዊ የአይሁድ እምነት ተከታይ፣ እምነቱ በሚፈቅደው መሠረት የተዘጋጀን ምግብ ለእየሩሳሌም እና ሃይፋ ገበያ በተሳካ ሁኔታ ማቅረቡን በማሕበራዊ መድረክ ማሳወቁን ተከትሉ፣ ክርክሩ ሞቅ ሊል ችሏል።
ኢስላማባድ የሚገኙ ባለሥልጣናት በበኩላቸው፣ ምግቡ የተላከው በሦስተኛ ሀገር በኩል መሆኑን እና ግለሰቡ በራሱ ያደረገው ጥረት እንደሆነ፤ በመሆኑም ከእስራኤል ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት መኖሩን እንደማያሳይ ተናግረዋል።
ቅዳሜ ዕለት የጀመረው ግጭት ግን የፓኪስታን እና እስራኤል የወደፊት ግንኙነትን በተመለከተ የሚደረገውን ክርክር ቢያንስ ለግዜው አስቁሞታል።
“በጋዛ የሚደረገው ጦርነት ያስተማረን የመጀመሪያ ትምህርት፣ በፓኪስታን የእስራኤልን እውቅና በተመለከተ የሚደርገውን ውይይት መቅበሩን ነው። ትክክልም ነው” ብለዋል፣ ሙሻሂድ ሁሴን የተባሉ እንደራሴ እና በፓኪስታን ፓርላማ የመከላከያ ኮሚቴ ሊቀመንበር።
“የሚያነጋግር ጉዳይም አልነበረም። ሌሎች አረብ ሀገራት ስላደረጉት ብቻ፣ ፓኪስታንም ታድርግ ማለት አይቻልም። እኛ ጉዳዩን በተመለከተ የራሳችን እይታ አለን። ይህም ከአረብ ሀገራት ይልቅ ለረጅም ግዜ የቆየና ያልተቀየረ ነው” ሲሉም አክለዋል እንደራሴው።
ማሊያሃ ሎዲ የተብሉ በአሜሪካና ተመድ የቀድሞ የሃገሪቱ አምባሳደር ደግሞ፣ ግንኙነትን በማሻሻል ላይ ለመነጋገር ግዜው አሁን አይደለም ብለዋል።
“በፓኪስታን፣ ልክ እንደ አረቡ ዓለም ሁሉ፣ ለፍልስጤም ያለው ድጋፍ ጠንካራ ነው” ሲሉ ሎዲ ለቪኦኤ ተናግረዋል። “ፓኪስታን ያለማወላወል ፍልስጤምን ስትደግፍ ነበር። ግጭቱ ሲረግብ ማየት ትሻለች” ሲሉ አክለዋል ሎዲ ።
በፍልስጤም ጉዳይ ምክንያት፣ በፓኪስታን ያሉ እስላማዊ ቡድኖች እና ቀኝ አክራሪ ፓርቲዎች ከእስራኤል ጋር ግንኙነት መፍጠር በሚለው ላይ ጠንካራ ተቃውሞ አላቸው።
በካራቺ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች የእስራኤልን ጥቃት በመቃወም እና ከፍልስጤም ጋር ያላቸው አንድነት ለመግለጽ ሰልፍ አድርገዋል።
የፓኪስታን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሃማስን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፣ ገለልተኛ አቋም የያዘ አስተያየት ሰጥቷል። “በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ሁኔታ በቅርብ እየተከታተልን ነው፣ የተባባሰው ሁኔታ የሚያስከትለው የሰው እልቂት ያሳስበናል” ብሏል የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ባወጣው መግለጫ።
የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ “ግጭቱ እንዲቆም፣ ሲቪሎች እንዲጠበቁ እና በመካከለኛው ምስራቅ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ” በአንድነት እንዲሠራ ጠይቋል።
በእስራኤል ላይ ያላትን ፖሊሲ በተመለከተ ‘ለውጥ እንደሌለ’ ፓኪስታን ማስታወቋ
የእስራኤሉ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ኤሊ ኮኸን በቅርቡ በተደረገው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን ለጋዜጠኞች ሲናገሩ እንዳሉት፣ ሀገራቸው ከሳዑዲ አረብያ ጋር የሰላም ስምምነት ብትፈርም፣ “ስድስት ወይም ሰባት” የሚሆኑ እስላም ሀግራት ከእስራኤል ጋር “ሰላም ይፈጥራሉ” ብለዋል።
“ከሳዑዲ ጋር ሰላም ተፈጠረ ማለት፣ ከእስልምናው ዓለም ጋር ሰላም ተፈጠረ ማለት ነው” ሲሉ አክለዋል።
ኮኸን የሰጡት አስተያየት ከፓኪስታን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጃሊል አባስ ጂላኒ ወዲያውን መስል አስከትሏል። ሀገራቸው ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ከሚሹ ሀገራት አንዷ ልትሆን ትችላለች የሚለውን ንግግር ውድቅ አድርገዋል።
“እስራኤልን በተመለከተ በፖሊሲያችን ላይ ምንም ለውጥ የለም። ለመለወጥ እያሰብንም አይደለም። ምንም ዓይነት ውሳኔ ስናደርግ፣ የሀገራችንን ጥቅም ከምንም በላይ እናስቀድማለን” ሲሉ ተደምጠዋል ጂላኒ በቅርቡ ኢስላማባድ ውስጥ በተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ።
ፓኪስታን ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላት ሲሆን፣ የኢኮኖሚ ችግሯን ለማስተንፈስ፣ ዳጎስ ያለ የገንዘብ ድጋፍ፣ እንዲሁም በረጅም ግዜ የሚከፈል የነዳጅ አቅርቦት ታገኛለች፡፡
በፓኪስታን ፖለቲካ ላይ አስተያየት የሚሰጡትና የሰላም አቀንቃኙ አህመድ ቁራዪሺ እንዳሉት ደግሞ፣ የጋዛው ግጭት በአረቡ ዓለም እና በእስራኤል መካከል የሚደረገውን የግንኙነት መሻሻል ጥረት እንዲያዘግም ሊያደርገው ይችላል፣ ምክንያቱ ደግሞ፣ መንግስታቱ ፖሊሲያቸውን ለማሻሻል በሚሞክሩበት ግዜ፣ የሕዝቡን አስተያየት ከግምት ውስጥ ማስግባት ስላለባቸው ነው ብለዋል።
“የሐማስ ወታደራዊ ቡድን ያባባሰው ግጭት፣ ሰላምን በቀጠናው ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ይጎዳዋል፣ የአስታራቂዎቹንም ስራ ያወሳስበዋል” ሲሉ ቁራዪሺ ለቪኦኤ ተናግረዋል።
“ነገር ግን፣ ግንኙነት የማሻሻሉ ሥራ አሁን የሚቆም አይመስልም። እንደውም ሐማስ ያሳየው፣ ግንኙነትን የማሻሻሉ ሥራ በአጣዳፊ መደረግ ያለበት መሆኑን ነው። ምክንያቱም፣ ነውጠኛ ቡድኖች፣ ቀጠናዊ ግጭትን ለሽብር እና ለተዘዋዋሪ አጀንዳ ማስፈጸሚያ መጠቀሚያ ሊያደርጉት ይችላሉ” ሲሉ ተከራክረዋል። “ሁሉም የፍልስጤምን መብት ይደግፋል። ትክክልም ነው። ነገር ግን፣ ሐማስ አስቸጋሪ ነውጠኛ ቡድን ነው፣ ወይንስ የፍልስጤምን አቋም የሚወክል ነው በሚለው ላይ ክርክር አለ” ሲሉም አክለዋል።
በአሜሪካ የተመራው የምዕራቡ ዓለም በሩሲያ ወረራ የተፈጸመባትን ዩክሬንን መደገፉን፣ በተቃራኒው ፍልስጤማውያን እስራኤል መሬታቸውን እንድትለቅ መጠየቃቸውን አለመደገፉን እንደራሴው ሙሻሂድ ሁሴን ነቅፈዋል።
“የምዕራብ ሀገራት እና በምዕራብ ያሉ የእስራኤል አዛኞች ድርብ መሥፈርት ነው ያላቸው። ግብዝነት ይታይባቸዋል። አቋማቸው በመርህ ላይ የተመሠረተ አይደልም። ሰብዓዊ መብትን እና ዲሞክራሲን የሚጠቀሙት፣ ለስልታዊ የውጪ ፖለቲካቸው መሣሪያ እንዲሆናቸው ነው። ከመርህ አንጻር ግን አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል እንደራሴው።
የፖለቲካ ተንታኙ ቁራዪሺ እና ፓኪስታናዊው አይሁድ ቤንክሃልድ፤ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸውና 15 የሚሆኑ የሰላም አቀንቃኞች ያሉበት ልዑክ ባለፈው ዓመት ወደ እስራኤል ያልተለመደ ጉብኝት ሲያደርግ፣ በቡድኑ ውስጥ ተካተው ነበር። ጉብኝቱ ከእስላም ሀገራት ጋር ግንኙነት እንዲሻሻል በሚሠራ የእስራኤል ድርጅት የተዘጋጀ ነብር።
“እኔ በፓኪስታን የምኖር ኩሩ ፓኪስታናዊ ነኝ። ከእስራኤል ጎን እቆማለሁ” ብሏል ቤንክሃልድ፣ በ X ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ቅዳሜ ግጭቱ ሲጀመር ባስተላለፈው መልዕክት፡፡ “የእስራኤል ወዳጆች እና የፍልስጤም አደራዳሪዎች በሁለቱም ወገን ያለውን ሰብዓዊ ስቃይ አሁኑኑ በአስቸኳይ እንዲያቆሙ ተስፋዬ ነው። ለማባባስ እና የሰላም ሂደቱን ለማጨናገፍ ሌላ ትንኮሳ መኖር የለበትም” ሲል አክሏል ቤንክሃልድ።
መድረክ / ፎረም