በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአወዛጋቢው የወልቃይት አካባቢ የተቋቋሙ አስተዳደሮች እንዲፈርሱ እየተሠራ መኾኑን መከላከያ ሚኒስትሩ ገለጹ


የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ / ፎቶ ፋይል
የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ / ፎቶ ፋይል

የትግራይ ክልልን መነሻ ያደረገውን ጦርነት ተከትሎ፣ በአወዛጋቢው የወልቃይት አካባቢ በአማራ ክልል የተመሠረቱ አስተዳደሮች፣ “ሕገ ወጥ በመሆናቸው” እንዲፈርሱ እየተደረገ ነው” ሲሉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ።

ሚኒስትሩ የአሸንዳ በዓልን አስመልክቶ፣ በፌስቡክ የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት፣ ከአወዛጋቢው አካባቢ የተፈናቀለውን ሕዝብ፣ በተደራጀ መልኩ በቅርቡ ወደ ቀዬው ለመመለስ እየተሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል።

ዶር. አብርሃም፣ “ሕገ ወጥ” ሲሉ የጠሯቸውን አስተዳደሮች የማፍረስና ሌላ የታጠቀ ኀይል እንዳይኖር የማድረግ ሥራ፣ በመከላከያ ሠራዊት እየተፈጸመ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በምትኩም ወደ ቀዬው የሚመለሰው ሕዝብ፣ መሪዎቹን በቀጥታ እንደሚመርጥ አመልክተዋል፡፡

ሕዝቡ ዝግጁ ሲኾን በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መሠረት፣ ጥያቄ በሚነሣባቸው የትግራይ አካባቢዎች፣ በሕገ መንግሥቱ እንደተደነገገው በሪፈረንደም ለመፍታት እንደሚሠራ ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡

ከሕግ እና ከሥርዐት ውጭ በጉልበት የሚንቀሳቀስ አላል ካለ፣ የፌዴራሉ መንግሥት የጀመረውን ሕግ የማስከበር ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል፣ ዶር. አብርሃም አሳስበዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ከአማራ ክልል እና ከፌዴራሉ መንግሥት ተጨማሪ አስተያየት እና ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለዛሬ አልተሳካም፡፡ ከጦርነቱ በኋላ፣ የዐማራ ክልል፣ “ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን” የሚለውን ጨምሮ፣ የተለያዩ የወረዳዎች አስተዳደሮችን ማቋቋሙ ይታወቃል፡፡

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ መሆናቸው የተነገረው ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን በእጅ ስልካቸው ላይ ብንደውልም፣ ስልካቸው ስለማይነሳ ምላሻቸውን ማካተተ አልቻልም።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG