በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዩናይትድ ስቴትስ የአየር ጥቃት የአልሸባብ ታጣቂዎች ተገደሉ


ታጣቂዎች በሶማልያ
ታጣቂዎች በሶማልያ

የዩናይትድ ስቴትስ ጦር በሶማሊያ አልሸባብ ተዋጊዎች ላይ ትናንት ሌሊቱን ባካሄደው ሦስት አዳዲስ የአየር ድብደባዎች 10 ታጣቂዎች መግደሉን አስታወቀ።

“በጋራ ራስን የመከላከል” የተሰኘው የአየር ጥቃት የተፈፀመው፣ በአልሸባብ የተጠመደውን የሶማሊያ ብሄራዊ ጦርን ለመደገፍ ነው ሲል፣ አፍሪኮም (AFRICOM) በመባል የሚታወቀው የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ወታደራዊ ዕዝ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በሶማሊያ የፌደራል መንግስት ጥያቄ የተፈፀመው የአየር ጥቃት የተካሄደው በታችኛው ጁባ ክልል ከኪስማዩ በስተሰሜን 105 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አፍማዶ ከተማ አቅራቢያ መሆኑን አፍሪኮም አስታውቋል፡፡

ከሶማሊያ ብሄራዊ ጦር ጋር በመተባበር ባካሄደው የአየር ጥቃት 10 የአልሸባብ አሸባሪዎችን መግደሉን የገለጸው አፍሪኮም፣ በጥቃቱ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ብሏል፡፡

የትናንቱን ቅዳሜ ሌሊት ጥቃት ጨምሮ በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት ሶማልያ ውስጥ በዩናይትድ ስቴትስ 13 የአየር ጥቃቶች መካሄዳቸው ተመልክቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለም በጁባ ላንድ ግዛት የደህንነት ኃይሎች የሚደገፈው የሶማልያ ጦር፣ ዛሬ እሁድ በአልሻባብ ቁጥጥር ስር ወደ ነበረችውና በታችኛዋ ጁባ ግዛት ወደምትገኘው ኻጋር ከተማ ዘልቆ መግባቱ ተገልጿል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG