በሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ከእሁድ ማለዳ ጀምሮ ለ72 ሰዓታት የሚቆይ ስምምነት ለማድረግ ተስማምተዋል። እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ሰብአዊ ርዳታ ለነዋሪዎች ለማድረስ ያስችላል ተብሏል።
“የሳዑዲ አረቢያ መንግስት እና ዩናይትድ ስቴትስ የሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች በመላው ሱዳን ተግባራዊ የሚሆን እና ለ72 ሰዓታት የሚቆይ ተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማታቸውን እናስታውቃለን” ይላል የሳዑዲ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ።
አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ ላለፉት ጥቂት ሳምንታት ሁለቱን ተፋላሚ ወገኖች ጀዳ ላይ ሲያወያዩ ሰንብተዋል።
ከስምምነቱ ተግባራዊነት በፊት በዋዜማው ቅዳሜ በካርቱም እና ኦምዱርማን ከተሞች ከፍተኛ የሆነ የአየር ድብደባ እና ውጊያ እንደነበር ነዋሪዎች ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ተናግረዋል።
ሚያዚያ 7 የጀመረውና ከሁለት ወራት በላይ የቆየው ግጭት ከ 2 ሺህ ሰዎች በላይ ሕይወት ሲቀጥፍ፣ 528 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ወደ ጎረቤት አገራት እንዲሸሹ አድርጓል። ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።
በሠራዊቱ መሪ አብደል ፋታህ አል ቡርሃን እና የቀድሞው የአል ቡርሃን ምክትል በሆኑት በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ መካከል የነበረው ፖለቲካዊ ፍጥጫ ወደ ጦር መማዘዝ ተሸጋግሮ፣ በተለይም የሱዳን መዲና ካርቱም እና በአካባቢዋ ያሉ ከተሞች ወደ ጦር አውድማነት ተቀይረዋል።
ከዚህ በፊት የደረጋሉ የተባሉ በርካታ የሠላም ስምምነቶች በሙሉ ከሽፈዋል።