►እንቅስቃሴው በአማራ ክልል ፈተና እንደገጠመው ገለጸ
►አብንና ባልደራስ፣ ጊዜውን ያልጠበቀ እና በአማራ ላይ ያነጣጠረ ነው፤ በሚል ተቃውመዋል
የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ዛሬ ማምሻውን በአወጣው መግለጫ፣ በኹሉም የአገሪቱ ክልሎች ያሉ የልዩ ኃይል አባላትን፣ ወደ ልዩ ልዩ የጸጥታ መዋቅሮች በማስገባት ላይ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
ይህም፣ “የአገሪቱን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት መጠበቅ የሚያስችል አንድ ጠንካራ የተማከለ ሠራዊት ለመገንባት በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ነው፤” ብሏል፡፡
“በኹሉም ክልሎች የሚገኙ የልዩ ኃይል አባላት እንደ ምርጫቸው እና እንደ ፍላጎታቸው፥ በመከላከያ፣ በፌዴራል ፖሊስ ወይም በክልል ፖሊስ አባልነት መካተት ይችላሉ፤” ያለው መግለጫው፣ “በዚኽ ሐሳብ ላይም ከልዩ ኃይል አመራሮች እና አባላት ጋራ ከመግባባት ላይ ተደርሷል፤” ሲል ገልጿል።
በመግለጫው እንደተጠቀሰው፣ ውሳኔው፥ በኹሉም ክልል አመራሮች ያለምንም ልዩነት ስምምነት ላይ ተደርሶበታል። “ይህን ተከትሎም ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፤” ነው ያለው፣ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን መግለጫ።
“ኾኖም፣ በአማራ ክልል በሚገኙ የተወሰኑ የልዩ ኃይል ክፍሎች ውስጥ፣ ሒደቱን የሚያውኩ ተግባራት ታይተዋል፤” ያለው የፌዴራሉ መንግሥት መግለጫ፣ ”ይህም የመልሶ ማደራጀት ሥራውንና ዓላማውን በአግባቡ ባለመረዳት፤ በሌላ በኩል ደግሞ፣ የጥፋት አጀንዳ አራጋቢዎች፣ ኾን ብለው በሚነዙት የሐሰት ወሬ በመጠለፍ” የመነጨ ነው ሲል አመልክቷል።
የሐሰት አጀንዳዎች በሚል ከጠቀሳቸው መካከልም፣ “የመልሶ ማደራጀቱ መርሐ ግብር፣ በአማራ ክልል ብቻ እየተካሔደ ነው፤ ህወሓት ትጥቅ ሳይፈታ እንዴት የክልሉ ልዩ ኃይል ትጥቅ ይፈታል የሚሉትና ሌሎችም ይገኙበታል፤” ብሏል።
ከአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና ከክልሉ የጸጥታ ቢሮ መረጃ ለማግኘት፣ ዛሬ ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ ትላንት በአወጣው መግለጫ፣ ገዥው ፓርቲ ውሳኔውን በአፋጣኝ እንዲቀለብስ አሳስቧል። የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን በድንገት እና ያለበቂ የጸጥታ ዋስትና ማፍረስ፣ ለጥቃት ተጋላጭ የኾኑ የአማራ ክልል አካባቢዎችን፣ ተገማች እና ቀጥተኛ ለኾነ ጥቃት ተጋላጭ የሚያደርግ ነው፤ በማለት አብን ውሳኔውን እንደሚቃወም ገልጿል።
ከአማራ ክልል መንግሥት እና ከክልሉ ሕዝብ ጋራ በጉዳዩ ላይ ውይይት እና ምክክር እንዲደረግና የክልሉንና የአገሪቱን ዘላቂ ሰላም በሚያረጋግጥ መልኩ ውሳኔው እንዲከለስ ሲልም ጥሪ አቅርቧል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲም፣ ውሳኔውን ተቃውሞ መግለጫ ያወጣ ሲኾን፣ “የፌዴራል መንግሥት የአማራ ልዩ ኃይል እንዲፈርስ ያስተላለፈው ውሳኔ፣ በኹሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች ላይ፣ በእኩል ደረጃ እና መጠን ተፈጻሚ በማይኾንበት ኹኔታ፣ የአማራን ሕዝብ ለጥቃት የሚዳርግ እኩይ ውሳኔ ስለኾነ፣ ውሳኔውን አጥብቄ አወግዛለኹ፤” ብሏል ባልደራስ በመግለጫው፡፡
“የክልል ልዩ ኃይል አባላትን ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች የማስገባት ፕሮግራም፣ በመላ አገሪቱ የሚተገበር ነው፤” ያለው የፌዴራሉ መንግሥት በበኩሉ፣ በአማራ ክልል የገጠሙኝ ፈተናዎች፣ ሒደቱን ለማደናቀፍ በሚፈልጉ ኃይሎች የሚከናወኑ ናቸው፤ ሲል ወንጅሏል።
በሌላ በኩል፣ “ህወሐት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት፣ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈታ እየተደረገ መኾኑ ሊታወቅ ይገባል፤” ሲልም ገልጿል።
በዚኽ ጉዳይ ላይ፣ የልዩ ልዩ አካላትን ሐሳብ ያካተተ ዘገባ በነገው ዕለት ይዘን እንመለሳለን፡፡