በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ስለ ትግራይ ደህንነት የመንግሥት መግለጫና የህወሓት ምላሽ 


ፎቶ ፋይል፡ የመቀሌ ከተማን የሚያሳይ ፎቶ/ ጥር/2013 ዓ.ም
ፎቶ ፋይል፡ የመቀሌ ከተማን የሚያሳይ ፎቶ/ ጥር/2013 ዓ.ም

የመንግስት ኮምዩኒኬሽንስ አገልግሎት ቅዳሜ ታኅሣስ 8/2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ “ የመከላከያ ኃይል ባልደረሰባቸው በአንዳንድ የትግራይ አካባቢዎች የኅብረተሰቡን ሰላም የሚነሡ የተደራጁ ዘረፋዎች እየተካሄዱ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ” ብሏል።

አገልግሎቱ “የሽግግር” ያለውን የአሁኑን ወቅት እንደ አጋጣሚ በመጠቀም፣ በተለይም በመቀሌ ከተማ በመንግሥትና በንግድ ተቋማት ላይ በፓትሮል የታገዘ ከፍተኛ ዝርፊያ መኖሩን መረጃዎች እየጠቆሙ ነው ሲልም አመልክቷል።

በዚህም “ሕዝቡ በከፍተኛ ምሬት ላይ መሆኑን በስልክና በሌሎችም መንገዶች እያሳወቀ ይገኛል” ሲል መግለጫው ጠቅሷል።

እየተፈጸመ ነው ላለው “ከፍተኛ ዝርፊያ” ማንነታቸውን በግልጽ ያልጠቀሳቸውንና “በሰላም ስምምነቱ ምክንያት ከግጭት የሚያተርፉት ትርፍ የቀረባቸው” ያላቸውን አካላት ተጠያቂ ያደረገው መንግሥት፣ ይህን ወንጀል የሚፈጽሙ ሁሉ ከተጠያቂነት አያመልጡም ሲልም አስጠንቅቋል፡፡

የህወሃት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ይህን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ አገልግሎት መግለጫ በትዊተር ገጻቸው አጋርተው በሰጡት አጭር ምላሽ፣ እኛና ሕዝባችን ልንፈታው የማንችለውን የትኛውንም የፀጥታ ስጋት፣ ማንም አይችለውም ብለዋል፡፡

ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በትግራይ ክልል ስላለው የፀጥታ ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግስት መግለጫ አውጥቶ ህወሃት ምላሽ ሲሰጥ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡

የመንግሥት መግለጫ እና አቶ ጌታቸው የሰጡት ምላሽ፣ ይዘታቸው ከሰላም ስምምነቱ ጋር ይቃረን እንደሆነ የጠየቅናቸው የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ዳዊት መሃሪ፣ መግለጫውም ይሁን ምላሹ “የሰላም ስምምነቱ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ለመሄዱ አመላካች ተደርገው የሚወሰዱ ነጥቦች አይደሉም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

እንደ አቶ ዳዊት አስተያየት በሰላም ስምምነቱ መሰረት የሚካሔደው የሽግግር ሂደት እስኪጠናቀቅ ድረስ፣ በትግራይ ክልል ሕወሓትም ሆኑ የፌዴራሉ መንግስት ተቆጣጥረው የሚገኙባቸውን አካባቢዎች ሰላምና ፀጥታ የማስከበር ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ከዚህ አኳያ፣ በሕወሓት ቁጥጥር ስር በሆኑት በመቀሌ ከተማ እና አካባቢው የደህንነት ችግር አለ ብሎ ካመነ መንግስት ደህንነቱን የማስጠበቅ ኃላፊነት ስላለበት “መግለጫውን ማውጣቱ የሚጠበቅ ነው” ይላሉ አቶ ዳዊት መሃሪ፡፡

የህወሃት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ስለሰጡት ምላሽም በሰጡት አስተያየት “አቶ ጌታቸው ችግሩ መኖሩን በምላሻቸው አልካዱም፤ ይልቁንም ምላሻቸው ከይዘቱ ይልቅ በቅርጹ የበለጠ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው” ብለዋል፡፡ ምክንያቱም “አቶ ጌታቸው እኛ መቆጣጠር የማንችለው፣ ህዝባችን መቆጣጠር የማይችለው፣ ሌላ አካል የሚቆጣጠርልን ስጋት የለም በሚል የሰጡት ጥቅል ምላሽ፣ አሁንም እኛ ጋር ኃይል አለ፤ ችግሮችን የመከላከል አቅምና ጉልበት አለን የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ይህ መልዕክት ደግሞ በዋናነት ለመንግስት ሳይሆን፣ ህወሃት ከውስጡም ይሁን በትግራይ ፖለቲካ ውስጥ “ህወሃት የሚጠበቅበትን አላደረገም፣ የህዝቡን ሰላም አላስጠበቀም፣ አቅም የለውም” ብለው ለሚተቹት አካላት ያስተላለፈው እንደሆነ ነው የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ዳዊት ያብራሩት፡፡

ይህ ማለት ግን “የሰላም ስምምነቶቹን ከመተግበር ሂደት ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ልዩነቶች አይኖሩም ማለት አይደለም” ያሉት አቶ ዳዊት፣ ልዩነቶች መኖራቸው እና መግለጫዎችን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች መገለጻቸው የሚጠበቅ እና ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ መሬት እስኪይዝ ድረስ፣ እሰጥ አገባዎች ይቀጥላሉ የሚል እምነት አላቸው፡፡

ይህ መሆኑ ግን፣ እርሳቸው እንዳሉት፣ የተጋነነ ልዩነትና ግጭትን የሚፈጥር ምክንያት የሚሆን አይደለም፡፡

በተለይ በመቀሌ ከተማ “በፓትሮል የታገዘ ዝርፊያ” እንደሚካሔድ መንግስት በመግለጫው መጥቀሱ ምን እንደሚያመለክት ጠይቀናቸው በሰጡት ምላሽ ፣ መንግስት መረጃዎቹ የደረሱት በስልክና በተለያዩ መሰል መንገዶች መሆኑን በመግለጫው መጥቀሱ እንዲሁም “በሰላም ስምምነቱ ምክንያት ከግጭት የሚያተርፉት ትርፍ የቀረባቸው” ያላቸውን አካላት ተጠያቂ ማድረጉ የሚሰጡት ትርጉም እንዳለ አብራርተዋል፡፡

መንግስት የጠቀሰውን ዘረፋ ሊያጣራ የሚችልበት አስፈላጊው መዋቅር በስፍራው የሌለው እንደመሆኑ፣ በስልክና በሌሎች መሰል መንገዶች የሚደርሱት መረጃዎች ምን ያህል ትክክለኛ ናቸው የሚለው፣ እንደ ተንታኙ አስተያየት፣ አጠያያቂ ነው፡፡ ስለሆነም፣ “ዘረፋውን የፈጸመውን አካል በርግጠኝነት መናገር አይቻልም” ባይ ናቸው አቶ ዳዊት፡፡

ነገር ግን ይላሉ፣ “ነገር ግን ከመንግስት ጋር የሰላም ስምምነት ያደረገና ተዋጊዎቹን ትጥቅ ለማስፈታት እንቅስቃሴ እያደረገ ያለ አካል በእንደዚህ አይነት ዘረፋ ውስጥ ይገባል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይመስለኝም” ብለዋል፡፡

አቶ ዳዊት አክለውም “ይሁን እንጂ፣ ይሄንን ተግባር ሊፈጽሙ የሚችሉ፣ የፖለቲካ ልዩነት ያላቸው የዛው ኃይል ታጣቂዎች ይኖራሉ” በማለት የመንግስትም መግለጫ ይሄንኑ እንደሚያመለክት ነው የገለጹት፡፡ የሰላም ስምምነቱን በመቃወም በተለያዩ አካባቢዎች ከመንግስት ጦር ጋር ውጊያ ሲያደርጉ የነበሩ ኃይሎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ይሄንንም ከዘረፋ ጋር በተያያዘ ለቀረበው ውንጀላ በማሳያነት አቅርበዋል፡፡

አቶ ዳዊት መሃሪ በመፍትሔነት ባቀረቡት ሃሳብ፣ “የመንግስት ወደ መቀሌ ከተማ መግባት ለብዙ ችግሮች መፍትሔ ሊሆን ቢችልም፣ ነገር ግን ‘ከሰላም ስምምነቱ ያፈነገጡ አካላት’ ሌላ የግጭት መንገድ እንዳይፈጥሩ በግልጽ ስምምነት መደረግ አለበት” ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በአንቀጽ 3 ላይ “በትግራይ ክልል ህዝባዊ አገልግሎቶችን ለማስጀመር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንዲሁም የከተማዋን ነዋሪዎች ደህንነት ለመጠበቅ የፌዴራል ኃሎች መቀሌ ከተማ እንዲገቡ ፓርቲዎቹ ተስማምተዋል” ይላል፡፡ ለዚህም ተግባራዊነት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና ሌሎች የፌዴራል ተቋማት፣ የሁለቱ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች በሚያደርጉት ግልጽ ግንኙነት አማካኝነት በሰላማዊና በተቀናጀ መልኩ በፍጥነት መቀሌ መግባት እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡

ይሁን እንጂ የፌዴራል መከላከያ ሰራዊት እና ሌሎች ተቋማት እስካሁን ወደ ከተማዋ መግባታቸው አልተገለጸም፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በቅዳሜው መግለጫው “የኢትዮጵያ መንግሥት ለሕዝብ እና ለሀገር ሰላም ሲባል በሰላም ስምምነቱ የገባውን ቃል ሳይውል ሳያድርና ሳያንጠባጥብ በመፈጸም ላይ ይገኛል” ብሏል።

ይሁን እንጂ፣ የትግራይ ክልልን በፕሬዝደንትነት በመምራት ላይ የሚገኙት የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፣ በህገወጥ ምርጫ የተቋቋመ ነው በሚል የፌዴራሉ መንግስት እውቅና ላልሰጠው የክልሉ ምክር ቤት እሁድ ታህሳስ 9/2015 ዓ.ም. ባደረጉት ንግግር፣ ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት በእነርሱ በኩል ኃላፊነታቸውን በሚገባ እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸው፣ የፌዴራሉ መንግስት ግን ጉድለቶች እንዳሉበት አብራርተዋል፡፡ ለዚህ ክስ ከፌዴራሉ መንግስት በኩል እስካሁነ በይፋ ምላሽ አልተሰጠም፡፡

XS
SM
MD
LG