በቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ አስተዳደር የወጣውና ፍልሰተኞች ድንበር ላይ ተይዘው እንዲመለሱ የሚያዘው ፖሊሲ በመጪው ረቡዕ ያበቃል፡፡ በዚህ የተነሳም ከፍተኛ ቁጥር ያላችው ፍልሰተኞች በዩናይትድ ስቴትስ ደቡብ ድንበር በኩል በመድረስ ላይ ናቸው።
በሺህ የሚቆጠሩ ፍልሰተኞች ሜክሲኮ ድንበር ላይ በምትገኘው ሲዩዳድ ኋሬዝ ከተማ በመሰባሰብ ወደ አሜሪካ ለመዝለቅ በዝግጅት ላይ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡
የአሜሪካ ህግ አውጪዎች እንዲሁም የጉምሩክና ድንበር ጥበቃ ባለስልጣናት ፖሊሲው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በመጪው ረቡዕ የሚያበቃ ከሆነ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ፍልሰተኛ ወደ ድንበር እንደሚመጣ እየተናገሩ ነው፡፡
በሺህ የሚቆጠሩትም ኤል ፓሶ ቴክሳስ ላይ ለአሜሪካ የጉምሩክና ድንበር ጥበቃ ባለስልጣናት እጃቸውን እየሰጡ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
እጃቸውን በመስጠታቸው፣ የፖለቲካ ጥገኝነቱን የማመልከቻ ሂደት እንደሚጀምሩም ተስፋ ያደርጋሉ።
ስደተኞቹ ኤል ፓሶ የደረሱት “ታይትል 42” በመባል የሚታወቀውና በቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ አስተዳደር የወጣው፣ ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚሞክሩ ፍልሰተኞች ከድንበር ላይ ተይዘው እንዲመለሱ የሚያዘው ፖሊሲ በመጪው ረቡዕ ሊያበቃ በተቃረበበት ወቅት ነው።
አንድ የዩናይትድ ስቴት ዳኛ ፖሊሲው በመጪው ረቡዕ እንዲያከትም ባለፈው ወር ውሳኔ ሰጥተዋል። ፖሊሲው የሚያበቃበት ጊዜ እስኪደርስም ፍልሰተኞቹ ሜክሲኮ ውስጥ ከአሜሪካ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ሲዩዳድ ኋሬዝ ከተማ በመሰባሰብ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡
ሁኔታው ከባድ እየሆነ እንደመጣ የቺኋኋ አገረ ገዢ ማሪያ ሁዌና ካምፖስ ጋልቫን ይናገራሉ።
ማሪያ በቅርቡ ለሪፖርተሮች ሲናገሩ አስፈላጊ ነገሮችን ሳያቀርብ የሜክሲኮ መንግስት ብሔራዊ ዘቡን በመጠቀም 1,500 የሚሆኑ ፍልሰተኞችን በአውቶብስ አሳፍሮ ወደ ሲዩዳድ ኋሬዝ ከተማ ማምጣቱን ነቅፈዋል።
ከዶሚኒካን ሪፐብሊክ የመጣው ፍልሰተኛ ጆወል ሞታ “እግዚአብሔር ይመስገን የሜክሲኮ ባለሥልጣናት ረድተውናል። በሰላም ደርሰናል። ግሩም አድርገው ተንከባክበውናል።” ብሏል፡፡ ከኒካራጓ የመጣው ኦስካር ሬየስም እንዲሁ“ያለፍንበት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነበር። ግን እግዚአብሔር ይመስገን የሜክሲኮ ህዝብ እጁን ዘርግቶ ተቀበለን። በሁሉም ነገር ረዱን፣ ምግብን ጨምሮ።” ብሏል፡፡
በሲዩዳድ ኋሬዝ ከተማ በሚገኝ መጠለያ ለጥቂት ሰዓታት ካረፉ በኋላ በመቶ የሚቆጠሩ ፍልሰተኞች ድንበር ላይ የሚገኘውን ሪዮ ግራንዴ ወንዝን ለመሻገር ወስነዋል። በመጠለያ ያሉ ባለሥልጣናት አላስቆሟቸውም።
“ማንም ኢዚህ እንዲቆይ የሚገደድ የለም። መረጃው ተሰጥቷቸው አውቀውት የሚወስኑት ውሳኔ ነው።” የሚሉት በመጠለያው የሚሠሩት አና ሎራ ሮዴላ ማስቆም አንችልም ይላሉ፡፡
ሮዴላ አያይዘውም “እንደ ደረሱ ምግብ ተሰጥቷቸው እንዲያርፉ ይደረጋል። ከዛም ሕጉ ይነበብላቸዋል። የሜክሲኮ መንግስት ሊያደርግላቸው ስለሚችለው ነገር ይነገራቸዋል። ከዛም እያንዳንዱ ቤተሰብ ማድረግ የሚፈልገውን ራሱ ይወስናል።” ብለዋል
በሺህ የሚቆጠሩ ፍልሰተኞች በሲዩዳድ ኋሬዝ ከተማና በኤል ፓሶ ከተሞች መሃል በሚገኘው ሪዮ ግራንዴ ወንዝ ላይ ለሚገኙ የዩናይትድ ስቴትስ ድንበር ጠባቂዎች እጃቸውን ሰጥተዋል። በኢል ፓሶ አካባቢ የድንበር ጠባቂዎቹ ቃል አቀባይ ኦርላንዶ ሩቢዮ እንዳሉት በቀን 2ሺህ 100 የሚሆኑ ፍልሰተኞች ይስተናገዳሉ።