በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሳማንታ ፓወር ከባድ የረሃብ ቀውስ የገጠመውን የአፍሪካ ቀንድ ጎበኙ


የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤሴአይዲ) አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር በኬንያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ / ሐምሌ 15/2014 ዓ/ም
የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤሴአይዲ) አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር በኬንያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ / ሐምሌ 15/2014 ዓ/ም

በሚሊዮን ለሚቆጠሩና ለተራቡ ህዝቦች አስፈላጊ የሆነውን የእህል አቅርቦት ከዩክሬን ወደቦች እንዳይወጣ ያገደውን የሩሲያ ወረራ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት እንዲቃወሙ የአሜሪካ የዕርዳታ ሃላፊዎች ጥሪ አቀረቡ።

ሃላፊዎቹ በተጨማሪም በኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን የሚገኙ የታጠቁ ቡድኖች በቁጥጥራቸው ስር ባደረጓቸው አካባቢዎች የምግብ ዕርዳታ እንዲያልፍ እንዲፈቅዱ ጥያቄ አቅርበዋል።

የአሜሪካ መንግስት ከፍተኛ የዕርዳታ ሃላፊዎች 20 ሚሊዮን ህዝብ ከረሃብ ጋር በተጋፈጠበት የምስራቅ አፍሪካ ክልል የሶስት ቀናት ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው። ሩሲያ ዩክሬንን በመውረሯና፣ ከሀገሪቱ ምግብ ወደ ውጪ እንዳይወጣ በመታገዱ፣ የምስራቅ አፍሪካውን ረሃብ እና የምግብ ዋስትና ችግር አባብሶታል።

“በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የ 1.2 ቢሊዮን ዶላር አዲስ ዕርዳታ ለኢትዮጵያ፣ ሶማሊያና ኬንያ በአንድ ላይ እንደተመደበ አሳውቄያለሁ። ዛሬ ደግሞ ገንዘቡ የምግብ ቀውስን ለመከላከል እንደሚውል አሳውቃለሁ። ይህ እጅግ በጣም ብዙ ገንዘብ ነው። እዚህ ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት የሚያሳይ ነው። ነገር ግን ሌሎች ለጋሾችም እጃቸውን እንዲዘረጉ እንፈልጋለን። በተመሳሳይ መንገድ፣ መድረስ የማይቻልባቸው አስቸጋሪ ቦታዎች ዕርዳታው እንዲደርስ ያሉንን ግብዓቶች ሁሉ ማንቀሳቀስ አለብን። ማንኛውም በግጭት ላይ ያለ ወገን የሰብዓዊ ዕርዳታው እንዳይደርስ እንቅፋት መሆን የለበትም” ሲሉ የአሜሪካ የዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ ሃላፊ የሆኑት ሰማንታ ፓወር ኬንያ መዲና ናይሮቢ ላይ ተናግረዋል።

ኬንያ ከዕርዳታው 255 ሚሊዮን ብር የደርሳታል። ወደ 4.1 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በኬንያ የምግብ ዋስትና የላቸውም። ይህም ባለፈው መጋቢት ከነበረው 3.5 ሚሊዮን ጭማሪ አሳይቷል። የኬንያ የህዝብ አገልግሉትና የጾታ ምኒስትር ማርጋሬት ኮቢያ እንዳሉት መንግስት በሀገሪቱ ደረቅና ከፊል ደረቅ በሆኑት አካባቢዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ አከፋፍሏል።

“መንግስት ካለፈው መስከረም ጀምሮ ገንዘብ እያከፋፈለ ይገኛል። ከቦታ ቦታ ተዘዋዋሪዎች ቢሆኑ እንኳ የእጅ ስልክ እስካላቸው ድረስ ገንዘቡ ይደርሳቸዋል” ብለዋል ምኒስትሯ።

በአፍሪካ ቀንድ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ረሃብ ጠርዝ የገፋ ድርቅ አጋጥሟል። የሰብዓዊ ድርጅቶች በኢትዮጵያም ሆነ በሶማሊያ እየተካሄዱ ባሉ ግጭቶች ምክንያት አንዳንድ የሀገራቱን አካባቢዎች ለማዳረስ ችግር ገጥሟቸዋል። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ደግሞ ምግብ፣ ውሃ እና መድሃኒት ለማግኘት ሲሉ ደህንነታቸው ወደሚጠበቅበት አካባቢ ለመሄድ ተገደዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ቱርክ ከዩክሬን እህል የሚወጣበትን መንገድ ለመፍጠር ከሩሲያ ጋር ስምምነት ለማድረግ ችለዋል። ሰማንታ ፓወር እንደሚሉት ግን ከዩክሬን የሚወጣው እህል ወደ ታቀደለት ስፍራ መድረሱን ለማረጋገጥ የአፍሪካ ሀገሮች ሩሲያ ላይ ግፊት ማድረግ አለባቸው።

“እህሉ ቢለቀቅም ለዚህ አካባቢ ይህ ወቅት የፈተና ግዜ ነው የሚሆነው። ነገር ግን በአህጉሪቱም ሆነ በዓለም ያሉ ሰዎች በአንድ ላይ ድምጻቸውን ለቭላድሚር ፑቲን ማሰማት አለባቸው፣ ‘እህሉን ይልቀቁ፣ እህሉን ይልቀቁ ሚስተር ፑቲን’ እያሉ ድምጻቸውን ማሰማት አለባቸው። ይህ በሂደት ላይ ያለ የሰብዓዊ ቀውስ ነው። ማናችንም ይህን ለማቃለል ማድረግ የምንችለው ካለ ማድረግ አለብን።

ሶማሊያ 90 በመቶ የሚሆነውን እህል ታገኝ የነበረው ከዩክሬን ነበር። ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ጭምር እህል ከገበያ መሸመት በጣም ውድ ሆኖባቸዋል። የዕርዳት ድርጅቶች እንደሚሉት በሶማሊያ 8 አካባቢዎች የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል። ከ7 ሚሊዮን ሰዎች በላይ በድርቅ ተጠቅተዋል። ድርቁ ከብቶችን ሲገድል፣ የግጦሽ መስክን አውድሟል።

XS
SM
MD
LG