በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ርዕሰ-አድባራት ደብረ-ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተ-ክርስቲያን፣ 25ኛ የብር ኢዮቤልዩ በዐል፣ ዋሽንግተን ዲ.ሲ


ቅድስት ማርያም ቤተ-ክርስቲያን
ቅድስት ማርያም ቤተ-ክርስቲያን
መሥራቾቿ እነ መጋቤ-ካህናት ከሀሊ ወንዳፈረው የዛሬ ፳፭ ዓመት፣ ደብረ-ሰላም ቅድስት-ማርያም ብለው ያቋቋሟት ይህች ቤተ-ክርስቲያን፣ በኋላ ነው፣ ሰፊ አገልግሎቷንና ቀዳማዊነቷን የተገነዘቡ ሁለት ብጹአን ሊቃነ-ጳጳሳት፣ አቡነ ይስሐቅና አቡነ ዜና-ማርቆስ በሕይወት በነበሩ ጊዜ «ርዕሰ-አድባራት» ብለው የሰየሟት።

በብዙ ሺህ የሚቆጠሩት ህፃናትን እያጠመቀች፣ የብዙ መቶ ወጣቶችን የጋብቻ በዐል በሥርዓተ-ተክሊል እየፈጸመች፣ ከዚህ ዓለም ለተለዩ አያሌ መቶዎች ፍትሐተ-ጸሎት እያደረሰ፤ ቀሪ ሕይወታቸውን በንጽሕና ለማሳለፍ ለወሰኑ ለብዙ ምዕመናንና ምእመናት የምንኩስና ማዕርግ እየሰጠች፣ ታዳጊ ወጣቶችን የሃይማኖት ትምህርትና የኢትዮጵያን ባህልከነ-ፊደሏ እያስተማረች፣ ጠቅላላ ምእመናኗን በቅዳሴና በጸሎት እያገለገለች እነሆ ለ፳፭ ዓመታት ተጉዛ እዚህ ደርሳለች።

ዋና አስተዳዳሪው ሊቀ-ማእምራን ቀሲስ ዶክተር አማረ ካሣዬ ደግሞ፣ የቤተ-ክርስቲያኒቱን የ፳፭ ዓመት ጉዞ፣ ከመንፈሳዊ አገልግሎጎቷ፣ ከንብረት ማግኘት ኃይሏ፣ ከአስተዳደራዊ እንቅስቃሴ እመርታዋና ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያውያን ጋር ካላት ቁርኝት አኳያ፣ በአራት ዐበይት ክፍሎች ያስቀምጡታል።

በንብረት እረገድ ከምንም ወይም ከባዶ የተነሳችው ይህች ቤተ-ክርስቲያን ዛሬ፣ በምእመናኖቿ እርዳታ በዋሽንግተን ዲሲ መሀል ከተማ፣ የተንጣለለ ሰፊ ቦታ ባለቤት ለመሆን በቅታለች ያሉት ሊቀ-ማእምራን ዶ/ር አማረ፣ የምታከራየው የራሷ ህንፃ እንዳላት፣ በአቅራቢያዋ ያለውን የጋዝ ማደያ ለመግዛት እየተደራደረች መሆኗንና በዚሁ ስፍራም አዲስ ህንፃ ለመገንባት ዕቅድ እንዳላት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በኤክኖሚው፣ በማህበራዊውና፣ የአገርንና የሕዝብን ህልውና የተመለከተ እስከሆነ ድረስ በፖለቲካውም ቢሆን፣ ሰፊ ተሳትፎ ማድረጓን ሊቀ-ማእምራን አብራርተዋል።

የ፳፭ኛው የብር ኢዮቤልዩ በዐል አዘጋጅ ኰሚቴ ሰብሳቢና የቤተ-ክርስቲያኒቱ አገልጋይ ካህን ቀሲስ ዘለዓለም አንተነህ፣ ኰሚቴው የተለያዩ መርሓ-ግብሮች በማውጣት፣ የበዐሉን አርማ በመምረጥና መሪ ቃሉንም በማዘጋጀ እንቅስቃሴውን የጀመረው ከ፮ ወራት በፊት መሆኑን ለቪኦኤ ገልጸው፣ የቤተ-ክርስቲያኒቱ ድረ-ገጽ ተሻሽሎ ካለፈው ሐምሌ ፲፭ ቀን ጀምሮ የተለያዩ ዝግጅቱን የተመለከቱ ፕሮግራሞች፣ እንደ ዐውደ-ርዕይ፣ የቤተ-ክርስቲያኒቱን አገልጋዮች ማስተወቅ፣ ልዩ የስብከተ-ወንጌል አገልግሎት፣ በጧፍ ማብራት ዝግጅት የሙታን መታሰቢያ ጸሎት፣ የስፖርት ዝግጅቶች፣ ወዘረፈ ሲተላለፉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

የዚህ ፕርግራም የመጨረሻ ግብና ዓላማ የነበረውም፣ የመሰረት ድንጊያ የማስቀመጥ ሥነ-ሥርዓት ሲሆን ያ ግን በዕለቱ አልተከናወነም። ምክንያቱም፣ የመሠረት ድንጊያ ያስቀምጣሉ ተብለው ይጠበቁ የነበሩ ብጹዓን ሊቃነ-ጳጳሳት ባለመገኘታቸው ነው። ይህን በተመለከተ፣ ተጠሪነቱ ለአባላት ምእመናን የሆነው የባለ-አደራዎች ቦርድ ዋና ጸሓፊ ወ/ ወሰንየለሽ ደበላ፣ በዕለቱ አንድ ልዩ መግለጫ አንብበው ነበር።

መግለጫቸው በጥቅሉ ሲታይ፣ ሊቃነ-ጳጳሳቱ የአየር ትኬት ተቆርጦላቸውና እሺታቸውን ሰጥተው ሲያበቁ ያልተገኙት በአካባቢያችን በተፈጠረና በሌሎችም አንዳንድ ምክንያቶች እንደሆነ ከመጠቆሙ ባሻገር፣ ብዙም ዝርዝር አልነበረውም። ወይዘሮ ወሰንየለሽ እንደተናገሩት ግን፣ የባለ-አደራዎች ቦርድ ወደፊት ሁሉንም በዝርዝር ለአባላትም ሆነ ለመላው ምእመናን ያሳውቃል።

please wait

No media source currently available

0:00 0:08:23 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ
XS
SM
MD
LG