በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

"አሊባባ በኢትዮጵያ"- ምጣኔ ሀብታዊ የምስራች ? ወይስ…


የአሊባባ ድርጅት ዋና መስሪያ ቤት ህንጻ
የአሊባባ ድርጅት ዋና መስሪያ ቤት ህንጻ
የ"አሊባባ" እና የኢትዮጵያ መንግስት ምክክር
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:56 0:00

ኢትዮ-ሱቅ የተሰኘውን የኢንተርኔት ላይ መገበያያ አውታር ለሚያስተዳድረው ቴዎድሮስ አበበ ፣የአጭር ጊዜ ልፋቱ በፈተና የተሞላ ነው፤‹‹እኛ ሀገር (የኢንተርኔት ላይ ግብይትን) የሚመለከት የንግድ ፈቃድ የለም፡፡ለግብይቱ አጋዥ የሆነ የአከፋፋል ዘዴንም ለማግኘት ያስቸግራል፡፡›› ይላል ቴዎድሮስ ከተጀመረ አንድ ዓመት ያስቆጠረ አገልግሎቱን መለስ ብሎ ሲያስታውስ፡፡

ከንግድ ፈቃድ አሰጣጥ ውጣ ውረድ እስከ ውጭ ምንዛሬ እጥረት ድረስ ከሚመዘዙ የዘርፉ ችግሮች ባልተናነሰ ቴዎድሮስን የሚያሳስበው ኢትዮጵያዊያን ለኢንተርኔት ግብይት ጽንሰ -ሀሳብ እንግዳ የመሆናቸው ጉዳይ ነው፡፡

ቴዎድሮስ ከሰሞኑ የሰማው ዜና ግን የምስራች ሆኖለታል፡፡ ከጓደኞቹ ጋር በትብብር የጀመሩት፣ሰዎች የተለያዩ ሸቀጦችን በኢንተርኔት በኩል የሚሸጡ እና የሚገዙበት ኢትዮ ሱቅን ለመጀመር መነሻ ካደረጓቸው ዓለማቀፍ አውታሮች መካከል አንዱ አሊባባ የተሰኘው የቻይናው ግዙፍ የኢንተርኔት ላይ ግብይት አውታር ነበር፡፡

አሊባባ ከፍተኛ አመራሮች ከኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች ጋር አብሮ ለመስራት ምክክር መጀመራቸውን ቴዎድሮስ በሰማ ቀን ፣ግዙፉ ድርጅት አገልግሎቱን ለማስተዋወቅ የሚፈጥረው ንቅናቄ ፣ በረከቱ ለጀማሪ ኢትዮጵያዊያንም እንደሚደርስ ተስፋ ሰንቋል፡፡

‹‹አሊባባ ኢትዮጵያ በሚመጣበት ጊዜ ሰዎች ትኩረታቸውን ወደ ( አውታሩ እንቅስቃሴ) የማድረግ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡እኛም በዚህ ሂደት የኢትዮጵያ ምርቶችን ለማቅርብ (ያስችለናል›› ፣ሲልም ያክላል፡፡

የቴዎድሮስ ተስፋ ግን፣ከስጋት የነጻ አይደለም ፡፡ወደ ስጋቱ እንመለሰላን፡፡ከዚያ በፊት ወደ ቻይና ሃንግዡ እናምራ፡፡

ሃንግዡ- ቻይና

በዚህ ሰሞን በደቡባዊ ቻይናይቱ የንግድ ከተማ ሃንግዡ ፣ዢዢ ወረዳ በሚገኘው የአሊባባ ቡድን ዋና መስሪያ ቤት ከተለያየ ዘርፍ የተውጣጡ ኢትዮጵያዊያን ባለስልጣናት እና ባለሀብቶች ከትመው ነበር፡፡

‹‹ከገንዘብ እና ኢኮኖሚ፣ከገቢዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ፣ከንግድ ባንክ ፣ከኢንደስትሪ እና አይቲ ፓርክ አስተዳደሮች … ከመሳሳሉት፤ በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ጽንሰ ሀሳብን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ተቋማት የተውጣጣ፣በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ጌታሁን መኩሪያ የሚመራ ልዑካን ቡድን አሁን በምንነጋገርበት ወቅት ስልጠና እየወሰደ ነው ፣›› በማለት የኢትዮጵያዊያኑ ባለስልጣናት በቻይና የመሰንበታቸውን ምክንያት የሚያብራሩት ፣በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ፤ከዚህ ስልጠና ቀደም ብሎ ፤በዳቮስ የዓለም የምጣኔ ሀብት ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የአሊባባ ቡድን ስራ አስኪያጅ ሚስተር ጃክ ማ ተገናኝተው ማውራታቸው የትብብር ምዕራፉን ከፋች አጋጣሚ እንደሆነም ያስታውሳሉ ፣‹‹ጃክ ማ፣ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩትን የለውጥ መርሃ -ግብር በጣም አድናቂ ስለነበሩ ፣አብረው ለመስራት መልካም ፍላጎታቸውን የገለጹበት ፣አሊባባ ቡድን ከሚሰራው [የኢንተርኔት ላይ] ንግድ ጋር በተያያዘ ለሀገራችን የሚጠቅሙ ነገሮችን ለመስራት የተስማሙበት አጋጣሚ ነበር፡፡››

ስታቲስታ የተሰኘው ዕውቅ መረጃ ሰብሳቢ እና አጣሪ ተቋም ይፋ እንዳደረገው አሊባባ ከ600 ሚሊየን በላይ የኢንተርኔት ላይ ገበያተኞች ያሉት አውታር ነው፡፡አራተኛው ግዙፍ የኢንተርኔት ላይ ተቋምም ነው፡፡

ከተመሰረተ 10 ዓመታትን የደፈነው ድርጅት፣ ዋነኛ ገበያተኞቹ ቻይናዊያን ቢሆኑም ፣ በመላ ዓለም ለሚገኙ ሸማቾች ዕቃዎችን ይሸጣል፣ቤታቸው ድረስ ይልካል፡፡ከሌሌች ተመሳሳይ አውታሮች በተለየ አሊባባ አንድ የንግድ ድርጅት ከሌላኛው ንግድ ድርጅት ጋር የሚያደርጋቸው የሸቀጦች ጅምላ ንግድ ይጧጧፍበታል፡፡ የንግድ ድርጅቶች በቀጥታ ከመደበኛ ሸማቾች ጋር የሚገናኙባቸው ገባር አውታሮችም እንዳሉት ሳይዘነጋ፡፡ከዚህ በተጨማሪ የኤሌክትሮኒክ ክፍያዎችን፣ጨምሮ የቴክኖሎጂ እና የሎጂስቲክ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡

‹‹ዲጂታል ኢኮኖሚን ለማሳደግ ፣የመንግስትን አገልግሎት በመረጃ ሳይንስ የተደገፈ ለማድረግ እና ለማዘመን በጠቅላይ ሚኒስትራችን በኩል ፍላጎት እንዳለ ይታወቃል፡፡ባለን ሀቅም የጀመርናቸው ስራዎች አሉን ፡፡ያንን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ሀሳቦች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡›› በማለት ኢትዮጵያ ከ አሊባባ ጋር የጀመረችውን የትብብር ምዕራፍ ዓለማ የሚስረዱት አምባሳደሩ ፣ዘመኑ ያመጣውን ዕድል ‹‹ቀልጠፍ ብሎ›› በመጠቀም ፣በአነስተኛ እና ጥቃቅን አምራችነት ዘርፍ ላይ የሚሰሩ አርሶ አደሮች ምርቶቻቸውን ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡበት ዕድል ለመፍጠር ውጥን መኖሩንም ያወሳሉ፡፡

በዶ/ር ጌታሁን መኩሪያ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ፣ከአሊባባ ዋና ስራ አስኪያጅ ጃክ ማ ጋር
በዶ/ር ጌታሁን መኩሪያ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ፣ከአሊባባ ዋና ስራ አስኪያጅ ጃክ ማ ጋር

ሎንዶን ፣እንግሊዝ

የኢትዮጵያን እና የቻይናን ምጣኔ ሀብት ነክ ግንኙነት በአንክሮ የሚከታተሉት የንግድ እና ምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ተንታኙ አብዱል መናን መሃመድ የኢትዮጵያ እና የአሊባባ ሰሞነኛ ጉድኝት ጥያቄ ያጭርባቸዋል፡፡

የኤደን ብራ የንግድ ትምህርት ቤት የኢንደስትሪያል ፖሊሲ የዶክትሬት ተማሪው አብዱል መናን ፣የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግብርና ላይ በእጅጉ መመስረቱን እያነሱ ኢትዮጵያ የአሁኑን ትብብር የፈለገችበትን ጊዜ ትክክለኝነት ይጠራጠራሉ፡፡

‹‹ኢትዮጵያ በዋናነት የግብርና ሀገር ናት፡፡ማኒፋክቸሪንጉ ገና አላደገም ፣ቀጥሎ የሚመጣው የአገልግሎት ዘርፉ ነው፡፡ማንበብ እና መጻፍ የማይችል ብዙ የማህበረሰብ ክፍል አለ፡፡እንዲህ አይነቱ [የኢንተርኔት ግብይት] ዘርፍ ጥሩ የኢንተርኔት [ትስስር] አገልግሎት ፣የነቃ እና የተማረ የህብረተሰብ ክፍል የሚጠይቅ ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ሁኔታ ነው አሊባባ እንደሚገባ የሰማነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት እና በምን ሁኔታ ውጤታማ እንደሚሆን ለእኔ አጠያያቂ ነው፡፡›› ይላሉ፡፡

አብዱል መናን ኢትዮጵያ ከአሊባባ ድርጅት ጋር የምታደርገው ውይይት እና መጪ ጊዜ ስምምነት ፣በዘርፉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ወጣኒ ኢትዮጵያዊያን ጭልጭል የሚል እንዳያዳፍነውም ይሰጋሉ፡፡

አዲስ አበባ -ኢትዮጵያ

በኢንተርኔት ላይ የንግድ እንቅስቃሴ ዘርፍ እየጣረ ያለውን የኢትዮ ሱቅ ስራ አስኪያጅ ቴዎድሮስን አበበን በድጋሚ አገኘነው፡፡

ቴዎድሮስ የአሊባባ ወደ ኢትዮጵያ ፊቱን ማዞር የፈጠረው ተስፋ ከስጋት የጸዳ አለመሆኑን ያስረግጣል፡፡ አሊባባ በዘርፉ እጅግ የጎለበተ እና ዋጋቸው ርካሽ የሆኑ ዕቃዎችን በቀላሉ ማዳረስ የሚችልበት ሀቅም ያለው አውታር ሆኑን በማንሳት በግዙፉ ድርጅት እና በወጣኒ ድርጅቶች መካካል የሚኖረው ፉክክር ተማዛኝ እንደማይሆን ፣የመዋጥ ዕጣፋንታ ሊከተል እንደሚችል ያወሳል፡፡

በዚሁ በአዲስ አበባ ፣በዲጂታል ንግድ ዘርፍ ፣እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ስፓት ላይት የተሰኘ ድርጅት ሃላፊ የሆነው ሳሙኤል በቀለ ግን ፡፡‹‹ውድድር አያስፈራንም!›› ይላል፡፡

የአሊባባ እግር ኢትዮጵያን ሲረግጥ በእሱ እና መሰሎቹ ላይ የሚተወውን የፉክክር ጫና ባይዘነጋም በሰበብ አስባቡ ለሚንገላታው ሸማች ግን አንጻራዊ እፎይታን እንደሚፈጥር ይሟገታል፡፡

‹‹ገበያን የመቆጣጠር፣ የሰራተኛ ሃይሉን የመበዝበዝ ሁኔታዎችም(በሌሎች ሀገራት) ይታያሉ፡፡እንደዚያም ሆኖ ግን፣እንደ እኛ ያለው ድርጅት ውድድር ያበረታታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም እየተጎዳ ያለው ተጠቃሚው(ሸማቹ ነው) ነው፡፡እነዚህ ሰዎች [አሊባባ] አልግሎታቸው ኪስን የማይጎዳ ነው፡፡ በዝቅተኛ ዋጋ ለተጠቃሚው በጣም የተሻሉ ምርቶችን ያቀርባሉ፡፡›› የሚለው ሳሙኤል ፣ከዚህ አልፎ የተጀመረው ጉድኝት ለቴክኖሎጂ ሽግግር ያለውን መልካም አጋጣሚም ይጠቅሳል፡፡

አንድ የአሊባባ ሰራተኛ በስራ ላይ ፣ቤጂንግ ቻይና
አንድ የአሊባባ ሰራተኛ በስራ ላይ ፣ቤጂንግ ቻይና

ለዚህ ዘገባ ምልከታቸውን ያበረከቱ ሁሉ የሚስማሙበት አንድ ነጥብ ቢኖር በኢትዮጵያ እና በቻይናው አሊባባ ቡድን መካከል የሚደረገው የመጪ ዘመን ምክክር በጥንቃቄ ፣የኢትዮጵያዊያንን ጥቅም ያስቀደመ እና የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብታዊ ግብ ያጤነ መሆን እንደሚገባው ነው፡፡

በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ግን የግዙፉ ኢንተርኔት ላይ ግብይት አውታር አሊባባ እና የኢትዮጵያ መንግስት በጋራ መስራታቸው አንዳች አሉታዊ ተጽዕኖ አይኖረውም ይላሉ፡፡በሚደረጉ ውይይቶች ውስጥ ከግሉ ዘርፍ የተወከሉ ወገኖችን መሳተፋቸው ይሄኑ ለማረጋገጥ እንደሆነ ይሟገታሉ፡፡

የቻይና መንግስት እና ቻይናዊያን ኩባንያዎች ከአፍሪካዊ ሀገራት ጋር የሚያደርጓቸው ማናቸውም ግንኙነቶች ከምጣኔ ሀብት ጥቅቅሞሹም በላቀ ፖለቲካዊ አንድምታ እንዳላቸው ደጋግመው የሚያነሱት የንግድ እና ምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ተንታኙ አብደልመናን መሀመድ ግን መጪው ጊዜ ይዞት የሚመጣውን በአንክሮ መጠበቅ እንደሚሻል ይመክራሉ፡፡

የአሊባባ ቡድን ሃላፊ ሚስተር ጃክማ ከሁለት ዓመታት በፊት የተለያዩ አፍሪካ ሀገራትን ከጎበኙ ወዲህ ግዙፍ ድርጅት ትኩረቱን በአህጉሪቱ ላይ አድርጓል፡፡

ባሳለፍነው የአውሮጳዊያን ዓመት አጋማሽ ላይ ኤስ ኤን ቢ ሲ ከተሰኘው የዜና ተቋም ጋር ቆይታ ያደረጉት የድርጅቱ ምክትል ፕሬዚደንት ብሪያ ዋንግ ፣የድርጅታቸውን የአፍሪካ ውስጥ እንቅስቃሴ ባብራሩበት ቆይታቸው ፣ በየትኛውም ቦታ የሚገኙ አነሰተኛ እና መካከለኛ የንግድ ድርጅቶች አውታሩን መሰረት አድርጎ በማስተሳሰር ለድርጅቱም ሆነ ለሌሎች የሚተርፍ የተሻለ የተጠቃሚነት ዕድል የመፍጠር ግብ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የአሊባባ ድርጅት መስራች ጃክ ማ መጪው ህዳር ላይ ኢትዮጵያ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ማስታወሻ፡- ለዚህ ዘገባ ሀሳባቸውን የበረከቱት ሰዎች የተጠቀሟቸው እንግሊዝኛ ቃላትን በአቻ አማርኛ ትርጉማቸው ለመተካት ጥረት ተደርጓል፡፡

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG