በትግራይ ክልል “አላማጣ ከተማ ላይ የመንግሥት ኃይሎች ትናንት በጄትና በድሮን ድብደባ ፈፅመዋል” ሲል ህወሓት ዛሬ በፅሁፍ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። መግለጫው አክሎም በስድስት ዙር ተካሄደ ባለው ድብደባ የ28 ስው ህይወት እንደጠፋ ተናግሯል።
የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ አገልግሎት ለዚህ ክሥ ቀጥተኛ ምላሽ ባይሰጥም ቀደም ሲል የተነሱ ውንጀላዎችን የሚያስተባብል መግለጫ ማምሻውን አውጥቷል።
ድብደባው የተፈፀመው በገበያ ማእከልና ሆቴል ላይ መሆኑን እስከአሁን ቢያንስ 76 ሰዎች መቁሰላቸው መታወቁንም ገልጿል።
መቀሌ የሚገኘው ሪፖርተራችን ሙሉጌታ አፅብሃ ያነጋገራቸው የዐይን እማኝ እንደሆኑ የተናገሩ ሰዎች በጥቃቱ ንብረትም እንደወደመ ተናግረዋል።
ይኸው የህወሓት መግለጫ አያይዞም “ድብደባው የተፈፀመው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር ስብሰባ በጠራበት ጊዜ መሆኑን” ጠቁሞ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች መንግሥቱ በሚፈፅማቸው የአየር ጥቃቶች “ሲቪሎች ላይ የህይወትና የአካል ጉዳት እየደረሰና መሠረተ-ልማት እየወደመ” ነው ብሏል።
ህወሓት አክሎም ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ መንግሥትና “አጋዥ” ባላቸው አጋሮቹ ላይ ተፅእኖ እንዲያሳድር አሳስቧል።
በክልሉ ውስጥ ባለው የትራንስፖርትና የስልክ ችግር ምክንያት ምክንያት በአላማጣ ላይ ተፈፅሟል የተባለውን ጥቃት በአካል ተገኝቶ ለማጣራት አለመቻሉን ሪፖርተራችን ሙሉጌታ ገልጿል።
ስለሁኔታው ከመንግሥቱ ባለሥልጣናት ምላሽ ለማግኘት ጥረት እያደረግን እንገኛለን። ዛሬ ያደረግናቸው ተከታታይ ጥረቶች አልተሳኩም። ይሁን እንጂ የኮምዩኒኬሽንስ አገልግሎቱ “የፈጠራ ቅጥፈቶች ለጊዜው ቢያደናግሩም፣ እውነት የመሆን ዐቅም ግን የላቸውም” በሚል ርዕስ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ህወሓት ትግራይ ውስጥና አጎራባቾቹ አማራና አፋር ክልሎች ውስጥ ፈፅሟቸዋል ያላቸውን ጥፋቶችና በደሎች ዘርዝሮ “አፈ ቀላጤዎቹ” ያላቸውን የምዕራብ ሚዲያና “አብረዋቸው በሰብዓዊ መብት ስም የሚሠሩ” ያላቸውን ተቋማት አውግዟል።
መግለጫው አያይዞም ሰሞኑን ምዕራብ ትግራይ ላይ ተፈፅመዋል ተብሎ በሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋማት የወጣውን ሪፖርትና የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች “የፈጠራ ክሥ” ሲል አስተባባሏል።
ለመንግሥቱ “የዜጎቹ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ቁልፍ አጀንዳ እንደሆነ” የሚናገረ ይኸው የኮምዩኒኬሽንስ አገልግሎቱ መግለጫ “ኢትዮጵያ የጀመረችው ለውጥ ሰው ተኮርና ለሰዎች መብትና ዕሴት ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጥ” ነው ብሏል።