የዛሬ ዓመት ከእስር የተለቀቀው የዞን ዘጠኝ የኢንተርኔት የጡመራ መድርክ አምደኛና የውይይት መጽሔት አዘጋጅ በፍቃዱ ኃይሉ ዛሬ በድጋሚ መታሰሩን ሌላዋ የኢንተርኔት አምደኛ ወ/ት ሶሊያና ሽመልስ ለአሜሪካ ድምጽ ገለጸች። የመታሰሩ ምክንያት ምን እንደሆነ እስክካሁን በግልጽ አለመታወቁን የገለጸችው ወ/ት ሶሊያና ከቤት የተወሰደው ግን የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን ለማስፈፀም በተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ትፈለጋለህ በሚል እንደሆን መረጃ እንዳላት ትናገራች።
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያዳምጡ
በፍቃዱ ኃይሉ በአዲስ አበባ በተለምዶ ፈረንሳይ እየተባለ በሚጠራው ቦታ በሚገኘው የቤተሰቦቹ መኖሪያ ቤት የሚኖር ሲሆን በአቅራቢያው ወደነበረው ፖሊስ ጣቢያ ተወስዶ ማቆያ ክፍል ለሰዓታት እንደቆየና እዚያ በነበረበት ወቅት ከቤተሰቦቹ ጋር እየተነጋገረ እንደነበረና እስከዛ ድረስ ምንም ዓይነት ጥያቄ እንዳልቀረበለት ወ/ት ሶሊያና ገልፃለች።
ወ/ት ሶሊያና ምንጮቿን ዋቢ አድርጋ ለአሜሪካ ድምጽ እንደተናገረችው በፍቃዱ ማምሻውን በተደረገለት አጠር ያለ የምርመራ መጠይቅ ስሙ ለተጠቀሰለት ብዙሃን መገናኛ ቃለ ምልልስ ሰጥተሃል የሚል ክስ በቃል እንደቀረበለት ነው።
የአሜሪካ ድምጽ ያነጋገራቸው የበፍቃዱ የቅርብ ወዳጆችም በተመሳሳይ ለምን ቃለ ምልልስ ሰጠህ በሚል እንደተጠየቀ ጠቁመዋል። ነገር ግን ወ/ት ሶሊያና እንደምትለው እስካሁን በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ላይ በክልከላ ከተቀመጡት ውስጥ በግልጽ ይህን ጥሰሃል ተብሎ የተነገረው ነገር እንደሌለ ነው።
በፍቃዱ ኃይሉ ዞን ዘጠኝ በተባለው የኢንተርኔት የጡመራ መድርክ ላይ በኢንተርኔት አምደኛነቱ ይታወቃል። በሚያዚያ ወር በ2007 እርሱና አምስት የኢንተርኔት አምደኞች ባሉበት ሌላዋ የኢንተርኔት አምደኛ ወ/ት ሶሊያና ሽመለስ በሌለችበት እንዲሁም ሦስት ጋዜጠኞችን ጨምሮ በሽብር ወንጀል ተከሰው ሲከራከሩ ከቆዩ በኋላ በመጀመሪያ አምስቱ ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር ሲለቀቁ ጥቂት ቆይቶ ደግሞ ሦስቱን እና ወ/ት ሶሊያና በሌለችበት ፍርድ ቤት በነፃ አሰናብቷቸው እንደነበር ይታወሳል።
በፍቃዱ ኃይሉን ግን አመጽ በጹሑፍ በማነሳሳት ክስ እዲከላከል ተበይኖበት በልደታ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የ20,000 ብር ዋስትና አሲዞ ከእስር እንዲፈታ ከሀገር እንዳይወጣ እገዳ ጥሎበት ነበር፡፡
በተጨማሪም በነፃ ከተሰናበቱት ሊሎች አራት አምደኞች አቤል ዋበላ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ አጥናፍ ብርሃነ እና ሶሊያና ሽመልስ(በሌለችበት)ጋር ዐቃቤ ህግ ይግባኝ ስለጠየቀባቸው ማክሰኞ ህዳር 6፣2009 ለአምስተኛ ግዜ ለብይን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በፍቃዱ ኃይሉ ዛሬ ስለታሰረበት ሁኔታ ከቤተሰቦቹ መረጃ ለማግኘት ጥረት አድርገን በፍቃዱ የታሰረው ለብዙሃን መገናኛ ቃለ ምልልስ ሰጥተሃል በሚል መሆኑን መስማታቸውን ገልጸው መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።
ጠበቃ እንዳለው ጠይቀን በዐአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ መሰረት ጠበቃ ማቆም ስለማይፈቀድ ለጊዜው ጠበቃ የለውም ስትል ወ/ት ሶሊያና ሽመልስ ገልፃልናለች።
ታሰረበት የተባለው የላምበረት አካባቢ የካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ስልክ ደውለን ስልኩን ያነሱት መሰረት የተባሉ ሴት በፍቃዱ ሃይሉ ተጫኔ ዛሬ የካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ መታሰሩንና የታሰረበትን ዝርዝር በተመለከተ ግን በአካል ቀርበን መርማሪውን ካልጠየቅን የሚነግሩን መረጃ እንደሌለ ገልጸዋል።
በፍቃዱ ኃይሉ ከእስር ከተፈታ በኋላ ውይይት የተሰኘ መጽሔት ከጓደኞቹ ጋራ በማዘጋጀት በማሳተም ላይ ይገኝ ነበር። በፍቃዱ ከባልደረቦቹ የዞን ዘጠኝ የድረ ገጽ አምደኞች ጋር በጋራ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሽልማቶችን አግኝቷል። ችልድረንስ ኦፍ ዜር ፓረንትስ (የወላጆቻቸዉ ልጆች) በሚል ርእስ በጻፈዉ ልብ ወለድ መጽሐፍም በግሉ ከአራት ዓመታት በፊት የአፍሪካ የስነጽሑፍ ሽልማት ውድድር ተወዳደሮ ሦስተኛ በመውጣቱ ተሸላሚ እንደነበር ይታወሳል።
ዝርዝሩን ከተያያዘው ድምጽ ያድመጡ