በወጣትነት ዘመናቸው በምድር ጦር፣ ሜታ አቦ እና መብራት ኃይልን በመሰሉ የኢትዮጵያ አንጋፋ የእግር ኳስ ክለቦች የተጫወቱት፤ አስከትለውም የስፖርት ጋዜጠኝነትን ዓለም የተቀላቀሉት ታሪኬ ቀጭኔን ከሚያሳስቧቸው ነገሮች አንዱ የቀድሞ የኢትዮጵያ ስፖርት ባለውለታዎች አስከፊ የህይወት ገጽታ ነው።
«ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ያስጠሩ ተቸግረው እየኖሩ ነው» ሲሉ ቁጭት በአዘለ ድምጸት የሚናገሩት ታሪኬ በረዳት ዕጦት ተገቢ ህክምና ባለማግኘታቸው ለከፋ ጤና የተዳረጉ ፣ ወደ ልመና ደጅ እስከመውጣት የደረሱ መኖራቸውን ያወሳሉ።
ቀደም ባለው ዘመን የነበረው የክፍያ ሁኔታ አንጋፋዎቹ ስፖርተኞች ሀብት እና ጥሪት እንዳይቋጥሩ እንዴት እንዳደረጋቸውም ሲያስረዱ « ስለገንዘብ የምታስብበት ጊዜ አልነበረም።ለምሳሌ እኔ ለምድር ጦር በምጫወትበት ጊዜ ደሞዛችን 105 ብር ነበር።ከዚያም ላይ 56 ብር ከ70 ለቀለብ ይቆረጥብን ነበር።
በዚያ ወቅት እነ አስፋው ባዩ ፣ሙሉዓለም እጅጉ ፣ ሙሉጌታ ብርሃኔ ፣ቡታ አስመሮም ፣ ወንድሙ ተክሉ (ካንጋሮ) ፣አረፋይኔ ምትኩ ፣በድሉ ሃይሌ እና በሃይሉ ቱራን የመሰሉ (አሁን በህይወት የሉም)።ይቺኑ ደሞዝ እያገኙ እየተጫወቱ፣ ስለገንዘብ የሚያስብ ፣የሚጠይቅ አልነበረም ።» ይላሉ ። ከተዘረዘሩት ተጨዋቾች አብዛኛው ኢትዮጵያን በአህጉራዊ እና ቀጠናዊ ጨዋታዎች ለድል ያበቁ እንዳሉ ልብ ይሏል።
የሜዳ ላይ ጓዶቻቸውን ተቸግረው ማየት ዕረፍት የነሳቸው የሚመስሉት ታሪኬ፣ደጋፊዎችን ማሰስ ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ከወዳጆቻቸው ያገኟቸውን ድጋፎች በህይወት ላሉ የቀድሞ ተጨዋቾች እና ከዚህ ዓለም ቀድመው ለተለዩት ቤተሰቦች አድርሰዋል።
ቀደም ብሎ ከአቶ ሸዋረጋ ደስታ(የቀድሞው የባንኮች ተጨዋች) በተገኘ ዋና ድጋፍ 10 የቀድሞ የክቡር ዘበኛ ፣ምድር ጦር፣ እና ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾችን እና ቤተሰቦቻቸው ለምግብ ፍጆታ እና ንጽህና መጠበቂያ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን እንዲያገኙ መደረጉን ነግረውናል።
የኮቪድ19 ወረርሽኝ ተከስቶ የብዙሃኑን ሃቅም መፈተን ሲጀምር በድጋሚ የቀድሞ የስፖርት ዓለም ባለንጀሮቻቸውን የሚደግፍ ሌላ ዙር ሰናይ ተግባር ማስተባባር አስፈልጓል። አንዳንዶቹ የሚገኙበት የጤና ሁኔታ አስከፊ መሆኑንም በማስረዳት የስፖርቱ ማህበረሰብ ትብብር አስፈላጊ መሆኑንም ያወሳሉ።
«በርካታ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን በዳኝነት የመሩት አቶ ዓለም አጽብሃ በስኳር በሽታ ምክንያት እግሮቻቸው (እንዲወገዱ) ተደርጓል፥በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እና የምድር ጦር ተጨዋች የነበሩት አበበ ጉርሙም ከስኳር በሽታ ጋር በተገናኘ (እግራቸውን አጥተዋል)። እነዚህን በህይወት ያሉ ሰዎች አለሁ ልንላቸው ይገባል።በህይወት የሌሊቱንም ቤተሰቦቻቸውን ማገዝ አስፋላጊ ነው» ሲሉም አክለዋል።
ከአንጋፋው የስፖርት ሰው ታሪኬ ቀጭኔ ጋር ያደረግነው ቆይታ አጥሮ ከስር ቀርቧል።
Your browser doesn’t support HTML5