የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን፣ ኢትዮጵያና የዓለም ማኅበረሰብ

  • ሰሎሞን ክፍሌ

የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን

የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት ሣይንስና ባህል ድርጅት፣ እንዲሁም ለነፃ ፕሬስ መከበር የቆሙ ሌሎች ድርጅቶች የዛሬውን ዓለምአቀፍ የፕሬስ ነፃነት ቀን ምክንያት በማድረግ የዓለም ጋዜጠኞች ደህንነት እንዲረጋገጥ ጥሪ አድርገዋል።



የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን


Your browser doesn’t support HTML5

የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን፣ ኢትዮጵያና የዓለም ማኅበረሰብ



የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት ሣይንስና ባህል ድርጅት፣ እንዲሁም ለነፃ ፕሬስ መከበር የቆሙ ሌሎች ድርጅቶች የዛሬውን ዓለምአቀፍ የፕሬስ ነፃነት ቀን ምክንያት በማድረግ የዓለም ጋዜጠኞች ደህንነት እንዲረጋገጥ ጥሪ አድርገዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣው ዘገባ ባለፈው የአውሮፓዊያን 2012 ዓመት ብቻ 121 ጋዜጠኞች እንደተገደሉ አኀዙም በቀደሙት ሁለት ዓመታት ከሞቱት እጥፍ እንደሆነ ገልጿል።

ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት - ሂዩማን ራይትስ ዋች በበኩሉ የዛሬውን የዓለም የነፃ ፕሬስ ቀን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያን ፀረ-ሽብር ህግ በመተቸት መግለጫ አውጥቷል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ በአቶ አንዱዓለም አራጌና በሌሎች ተከሣሾች ላይ ያፀናውን ፍርድ በመቃወም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት መግለጫ አውጥቷል፡፡

“የኢትዮጵያው ፀረ-ሽብር ሕግ የፕሬስ ነፃነትን አውድሟል” ይላል ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የሚሟገተው መንግሥታዊ ያልሆነ ነፃ ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዋች ያወጣው መግለጫ ርዕስ፡፡

በናይሮቢ-ኬንያ የድርጅቱ ጥናት አቅራቢ ለቲሺያ ቤደር መግለጫውን ሲያብራሩ “ዓለም የፕሬስ ነፃነትን አክብሮ በሚውልበት በዛሬው ቀን ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ጋዜጠኞች ታስረው እንደሚገኙና አንዳንዶቹም በአገሪቱ ፀረ-ሽብር ሕግ የተፈረደባቸው እንደሆኑ ይህ ሕግም ከረቂቁ ጀምሮ ፀድቆ ሕግ እስከሆነበት ጊዜ ድረስ አሳሳቢ መሆኑንና የመናገር መብትን የሚያፍን መሆኑን ነው የገለፅነው።” ብለዋል፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዋች እአአ ከ2011 ጀምሮ አሥራ አንድ ጋዜጠኞች /ስድስቱ በሌሉበት/ አፋኝ ባለው ፀረ-ሽብር ህግ ተከስሰው እንደተፈረደባቸው ይገልፃል።

በአሁኑ ወቅት በፀረ ሽብር ሕጉ የተከሰሱና ተፈርዶባቸው እሥር ቤት የሚገኙ ጋዜጠኞች በአጠቃላይ አምስት መሆናቸውን፤ እነርሱም እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ እና ውብሸት ታየ፣ እንዲሁም በፀረ-ሽብር ሕጉ ተከስሰው ፍርድ የሚጠባበቁ ሁለት ደግሞ ዩሱፍ ጌታቸውና ሰሎሞን ከበደ መሆናቸውን ለቲሺያ ቤደር ጠቅሰው የኢትዮጵያ መንግሥት የታሠሩትን በፍጥነት ከእሥር እንዲፈታ ጠይቀዋል።

“እአአ በ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፀረ-ሽብር ሕግ ከፀደቀ ወዲህ ነፃ መገናኛ ብዙኃንን አሳብቦ ለማሳደድ በያዘው ሕግ የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጦች ተንኮታኩተዋል” ይላል የሂዩማን ራይትስ ዋች መግለጫ፡፡

መንግሥት ሆን ብሎ ጋዜጠኞች እንዳያሣትሙ እንደሚያደርግ፣ በኢንተርኔት የሚተቹትን ጽሁፎች እንደሚጋርድ፤ የማስተዋል አሣታሚ ባለቤት የሆነውን ማስተዋል ብርሃኑን እና የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረውን ተመስገን ደሣለኝን በዚሁ ፀረ-ሽብር ሕግ ከስሦ እንደሚያጉላላ ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ ሂዩማን ራይትስ ዋች እና የጋዜጠኞች ደህንነት ተሟጋቹ ኮሚቴ - ሲፒጄ ያሉ ድርጅቶች የሚሠነዝሩበትን የመብት ጥሰት ነቀፋ አይቀበልም።

ባለሥልጣናቱ “ኔኦ-ሊብራልና የምዕራቡን የነፃነት ፍልስፍና ለማስፋፋት የሚሠሩ” ሲሉ ይተቿቸዋል፡፡ የአሁኑ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሣለኝ በአንድ ወቅት ስለሰብዓዊ መብቶችና የመናገር ነፃነት በአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ጋዜጠኛ ተጠይቀው “እኛ የምንከተለው የቻይናን ልማታዊ ዴሞክራሲ እንጂ የምዕራቡን ፍልስፍና አይደለም” ማለታቸውን ለሂዩማን ራይትስዋ አጥኚ አንስቼ ነበር።

“ጥሪአችን ስለ ርዕዮተ-ዓለም አይደለም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰለተደነገጉት የሰው ልጆች መብቶች እንጂ” ይላሉ ለቲሺያ ቤደር …
የሂዩማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ፕሮግራም ዳይሬክተርና የኢትዮጵያና የኤርትራ ጉዳዮች ኃላፊ ሌስሊ ሌፍኮ በበኩላቸው እአአ በ2007 ዓ.ም ኢትዮጵያ እሥር ቤት ውስጥ የሚገኙ ሁለት የኤርትራ ጋዜጠኞች ሳላህ ኢዲሪስ ጃማ እና ተስፋልደት ኪዳኔ ተስፋዝጊ ደህንነት ድርጅታቸውን እንደሚያሳስብ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የእነዚህን ሁለት ጋዜጠኞች በጠበቃ የመወከል መብታቸውን እንዲያከብር፣ እንደ ዓለምአቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ባሉ ነፃ አካላት እንዲጎበኙ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በሕይወት መኖራቸውን እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል።

በኤርትራ እስር ቤቶች ውስጥ ሰለሚገኙ ቁጥራቸው ከአሥር በላይ የሚሆንና ከአሥራ አንድ ዓመታት በላይ ስለታሠሩ ጋዜጠኞች አያያዝ ሲገልፁም የሚገኙት በመጨረሻው አስከፊ ደረጃ ላይ እንደሆነ ገልፀዋል።

“ሁሉም የታሠሩት ከስው ጋር እንዳይገናኙ በመደረግ በአስከፊ ሁኔታ ነው፤ አንዳንዶቹም ጋዜጠኞች እሥር ቤት ውስጥ መሞታቸውን ከተአማኒ ምንጮች ሰምተናል። አንዱ ለምሣሌ ጉዳዩ በጣም የታወቀው ዳዊት ይስሃቅ ነው …” ብለዋል፡፡

ተጨማሪና ዝርዝር ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡