ዩናይትድ ስቴትስ ዕዳዋን ለመክፈል ሪፐብሊካኑ ከጠርዘኛ አቋማቸው እንዲታቀቡ ባይደን ጠየቁ

Your browser doesn’t support HTML5

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ በጃፓን ሂሮሺማ የቡድን - 7 አባላት ስብሰባን ለማጠናቀቅ እየተዘጋጁ በነበሩበት ወቅት፣ ዩናይትድ ስቴትስ ዕዳዋን መክፈል እንድትችል፣ ሪፐብሊካን ፓርቲ ከያዙት ጠርዘኛ አቋማቸው እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ፣ በጃፓኑ የቡድን - 7 ስብሰባ ላይ ተገኝተው ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ዕዳዋን መክፈል እንዳትችል በሚያከላክላት መሰናክል ላይ የሚደረገው ንግግር ቀጥሏል፡፡

“በእኔ በኩል የድርሻዬን ተወጥቻለኹ፤” ያሉት ባይደን፣ “ከዚኽ ቀደም በገባኹት ቃል መሠረት፣ ከወጪ ቅነሳ እና ከዐዲስ ገቢዎች ጋራ በማጣመር፣ ወደ ሦስት ትሪሊዮን ዶላር ከሚጠጋ የጉድለት ቅነሳ በተጨማሪ፣ ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ለመቀነስ ዕቅድ አቅርቤያለኹ፡፡ አሁን ደግሞ መንቀሳቀስ ያለበት ሌላኛው ወገን ነው፤” ብለዋል፡፡

ሪፐብሊካኖች በበላይነት የሚቆጣጠሩትን የተወካዮች ምክር ቤት የሚመሩት፣ አፈ ጉባኤው ከቪን መካርቲ፣ ከፍተኛ የወጪ ቅነሳ ጥያቄ አቅርበዋል።

የተወካዮች ምክር ቤት አባል ጆዲ አሪንግተን፣ በኤቢሲ ቴሌቭዥን፣ “በዚኽ ሳምንት” ፕሮግራም ላይ ቀርበው፣ ለሀብታም ግለሰቦች እና ኩባንያዎች ተሰጥቶ የነበረውን የግብር እፎይታ በማንሣት ገቢን ለመጨመር የቀረበውን የባይደንን የበጀት ዕቅድ ተቃውመውታል፡፡

“እኔ እንደሚመስለኝ፣ የአሜሪካ ሕዝብ እየደረሰበት ያለው የኑሮ ውድነት ቀውስ የመነጨው፣ በወጪ ምክንያት እንጂ፣ አነስተኛ ግብር ስላለብን አለመኾኑን ይገነዘባል፡፡ እውነታው፣ በኮቪድ-19 ጊዜ የተገኘ ከፍተኛ የታክስ ገቢ የነበረ ሲኾን፣ እ.ኤ.አ. በ2021ም እንዲሁ የተመዘገበ ከፍተኛ የግብር ገቢ ተገኝቷል፤” ብለዋል ጆዲ፡፡

ዴሞክራቱ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ክሪስ ቫን ሆለንም እንዲሁ፣ በኤቢሲ ቴሌቭዥን ላይ በመቅረብ፣ “ዕዳን መክፈል አለመቻል ውስጥ ከገባን፣ የምናወራው፥ ስለ ኢኮኖሚው ድቀት ነው፡፡ የምንነጋገረው፥ ከሥራ ስለሚባረሩ ወደ 18 ሚሊዮን ሰዎች ነው፡፡ የምንነጋገረው፥ ስለሚጨምረው የወለድ መጠን ነው፡፡ የምንነጋገረው፥ ለአሜሪካውያን ሁሉንም የበለጠ እየተወደደ ስለመምጣቱ ነው፤” በማለት፣ ይከተላል ያሉትን ጉዳት አብራርተዋል፡፡

የብድር ጣራው ከፍ የማይል ከኾነ፣ ከባድ ምርጫዎች መደረግ ይኖርባቸዋል፤ ያሉት “ሚት ዘፕሬስ” በተሰኘው የኤንቢሲ ቴሌቭዥን የቀረቡት የገንዘብ ሚኒስትሯ ጃኔት ዬለን ናቸው፡፡

ዬሌን፣ “በዋናው ዕዳችን ላይ ወለድ መክፈል ይኖርብናል፡፡ በማኅበራዊ ደኅንነት ዋስትና ለሚተማመኑና ክፍያ ለሚጠብቁ የሠራዊቱ አባላት መክፈል ይኖርብናል፡፡ ለፌደራሉ መንግሥት አገልግሎት ለሚሰጡት የኮንትራት ሠራተኞች እና ለሌሎች አንድም የሚከፈሉ ክፍያዎች አይኖሩም፤” ብለዋል፡፡

እ.ኤ.አ እስከ ሰኔ ወር መጀመሪያ ድረስ፣ ሪፐብሊካኑና ዴሞክራቶቹ የምክር ቤት አባላት፣ ከአንድ ስምምነት የማይደርሱ ከኾነ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ምንም ገንዘብ እንደማይኖራት፣ የገንዘብ ሚኒስትሯ ጃኔት ዬለን አሳስበዋል፡፡