የርዳታ እህል ለተረጂ ያልደረሰው “በመጠነ ሰፊና የተቀናጀ ዘመቻ” እንደኾነ ዩኤስኤአይዲ አስታወቀ

Your browser doesn’t support HTML5

ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ የምትለግሰው የምግብ ርዳታ እንዲቋረጥ ያደረገችው፣ “ለተረጂው አይደርስም” በማለት እንደኾነ በይፋ አስታወቀች፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (USAID)፣ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው የምግብ ርዳታ፣ “ለተረጂዎች አይደርስም” ሲል፣ ርዳታውን ማቋረጡን፣ በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።

“ለተቸገረው የኢትዮጵያ ሕዝብ መድረስ የሚገባው የምግብ ርዳታ፣ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲቀየስ የሚያደርግ፣ መጠነ ሰፊ እና የተቀናጀ ዘመቻ መኖሩን”፣ ዩኤስኤአይዲ እና የኢትዮጵያ መንግሥት በመተባበር ባደረጉት ማጣራት ከድምዳሜ ላይ መድረሳቸውን፣ የድርጅቱ ቃል አቀባይ በይፋ በሰጡት መግለጫ አብራርተዋል።

ኾኖም፣ ርዳታው ለተረጂ ወገኖች እንዳይደርስ ከሚደረገው ዘመቻ ጀርባ ያለው ማን እንደኾነ፣ በመግለጫው ተለይቶ አልጠቀሰም። ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአፍሪካ ቀንድንና አካባቢውን ክፉኛ ከጎዳው ድርቅ እና በቅርቡ ከአበቃው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋራ በተያያዘ፣ ለርዳታ ጠባቂነት የተጋለጡትን ጨምሮ፣ ቁጥሩ 20 ሚልዮን ለሚደርሰው ተረጂ ሕዝብ ዋናዋ ለጋሽ ሃገር ናት።

ሮይተርስ የዜና ወኪል በተመለከተው እና በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ፣ የረድኤት ሥራ ለሚያከናውኑ የውጭ ለጋሽ ቡድኖች የቀረበ አንድ ሰነድ፣ “የርዳታ ምግቡ፥ ለአገሪቱ ልዩ ልዩ ወታደራዊ ክፍሎች እንዲሰጥ ተደርጓል፤” ብሎ፣ ዩኤስኤአይዲ እንደሚያምን ይጠቁማል።

ርዳታውን ከታለመለት ዓላማ ውጭ የማዋሉ ድርጊት፣ “በፌዴራል እና በክልል መንግሥታት አካላት የተቀነባበረ ዘመቻ፣ በመላ አገሪቱ የሚገኙ ወታደራዊ ክፍሎች፣ ለሰብአዊ ርዳታ የመጣው ምግብ ተጠቃሚ ናቸው፤” ሲል፣ ዩኤስኤአይዲ’ን ያካተተው ይኸው የለጋሾች ቡድን ሰነድ አመልክቷል።