በአሜሪካ ምርጫ ሁለተኛው ፕሬዚዳንታዊ ክርክር

  • ቪኦኤ ዜና

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እና ሪፐብሊካኑ ዕጩ ተፎካካሪያቸው ሚት ራምኒ

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እና ሪፐብሊካኑ ዕጩ ተፎካካሪያቸው ሚት ራምኒ በጉጉት ሲጠበቅ የሰነበተውን ሁለተኛውን ክርክራቸውን ማክሰኞ፣ ጥቅምት 6 ቀን 2005 ዓ.ም ምሽት ላይ አካሂደዋል፡፡



Your browser doesn’t support HTML5

ሁለተኛው ፕሬዚዳንታዊ ክርክር



በኒው ዮርኩ ሆፍስትራ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው በዚህ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ቅርፅ ባለው ክርክራቸው ወቅት በአዳራሹ ውስጥ ከተገኙ መራጮች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ እየሰጡ ነው ክርክራቸውን ያካሄዱት፡፡

ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል በኢነርጂ፣ በሃገሪቱ ምጣኔ ኃብት፣ በሥራ ዕድሎች ፈጠራና በሴቶች ለአንድ ዓይነት ሥራ አንድ ዓይነት ክፍያ፣ እንዲሁም የኢሚግሬሽን ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡

የመጀመሪያው ጥያቄ የቀረበላቸው ከአንድ የኮሌጅ ተማሪ ነው፡፡ “ስመረቅ ሥራ ይዤ እራሴን እንዲችል ምን ታደርጋላችሁ?” የሚል ነበር፡፡

ተማሪዎች ከኮሌጅ ሲወጡ ከዕዳ ቁልል ጋር መውጣታቸው፣ የሥራ ዕድሉ ግን የጠበበ መሆኑ ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ ነው ሲሉ ሚት ራምኒ መልሣቸውን ጀምረዋል፡፡ ተማሪው ዕድሉ ሰፊ ሊሆን የሚገባው ነው ብለው እንደሚያምኑ ነግረውታል፡፡ በዝርዝር አይናገሩት እንጂ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ተመልሶ ሊያድግ የሚችልበትን መንገድ እንደሚያውቁም አመልክተዋል፡፡



ፕሬዚዳንት ኦባማ በሰጡት መልስ ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ በዓለም እጅግ የላቀው ሥርዓተ ትምህርት ሊኖራት እንደሚገባ አመልክተው ከኢራቅና ከአፍጋኒስታን ጦርነቶች የሚያተርፉትን ገንዘብ ወደ ሥራ በማስገባትና አምራች የሥራ መስኮችን አሜሪካ ውስጥ በማበረታታት የበለጡ የሥራ ዕድሎችን እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል፡፡

ኢነርጂን በተመለከተ የኦባማ አስተዳደር ብዙ ፍቃዶችን ባለመስጠቱ ምክንያት የድፍድፍ ዘይት እና የጋዝ ቁፋሮና ልማት ሥራ ማዘቅዘቁን ሚስተር ራምኒ ቢገልፁም ፕሬዚዳንት ኦባማ ግን ይህንን የራምኒን አባባል አስተባብለው ፍቃድ የሚወስዱት ሁሉ ወደ ሥራ እንደማይገቡ አመልክተው በሌላ በኩል ግን ሚስተር ራምኒ የነዳጅ ኩባንያዎች የአሜሪካን ፖሊሲ ቀራጮች እንዲሆኑ ሊያደርጉ እንደሚፈልጉ በማንሣት ከስሰዋል፡፡



ሚስተር ራምኒ ለንፁህና ለታዳሽ ኢነርጂ ቦታ እንደማይሰጡ ኦባማ ቢናገሩም ራምኒ ግን የእርሣቸው አጠቃላይ የኢነርጂ ፖሊሲ ታዳሽ የኢነርጂ ምንጮችንም እንደሚያጠቃልል ገልፀዋል፡፡

ሚት ራምኒ የፕሬዚዳንቱን ባለፉ አራት ዓመታት የሥራ አፈፃፀም ላይ ጥቃት ከፍተው ሲያጣጥሉ “የሃገሪቱን የበጀት እጥረት በእጥፍ አሣድገዋል፤ ሲመረጡ እሠራለሁ ያሉትንም አልሠሩም” ብለዋል፡፡

“አሁን የሥራ አጥነቱ መጠን 5 ነጥብ 4 ከመቶ ይሆናል ብለው ነበር - አሉ ራምኒ በማከል የፕሬዚዳንቱን የዛሬ አራት ዓመት ቃል ሲያስታውሱ - በዚያ ቃል በገቡት 5 ነጥብ 4 ከመቶ እና ዛሬ ባለው የሥራ አጥነት መጠን መካከል የዘጠኝ ሚሊየን ሥራ አጥ አሜሪካዊያን ልዩነት አለ፡፡ የፕሬዚዳንቱ ዕቅድ ይህ ነበር፤ አልሠራም፡፡ የአረጋዊያን የጤና ጥበቃ ሥርዓትና የማኅበራዊ ዋስትና አያያዝ ወደ ውድቀት እያዘገሙ መሆናቸውን ጠቅሰው እስከአሁን ባለው ጊዜ የሚያሻሽል ዕቅድ አቀርባለሁ፤ አሻሽላለሁ፣ እጨርሣለሁ ብለው ነበር፤ እንኳን ሊሠሯቸው በአንዳቸው ላይ እንኳ ሃሣብ አላቀረቡም” ብለዋል፡፡



ፕሬዚዳንቱ በሰጡት የአፀፋ ምላሽ ቃል ከገቡባቸው ሥራዎች አብዛኞቹን መፈፀማቸውን ተናግረዋል፡፡ ያልፈፀሟቸውም ቢሆኑ ያልተሠሩት “ባለመጣራቸው ምክንያት እንዳልሆነ” ገልፀዋል፡፡

“የዛሬ አራት ዓመት - አሉ ኦባማ ለታዳሚው - ለአሜሪካ ሕዝብም፣ ለእናንተም እንዲህ ብዬ ነበር፡፡ መካከለኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰቦች ታክስ እቀንሣለሁ ብዬ ነበር፤ ቀንሻለሁ፡፡ ለአነስተኛ ንግዶች የታክስ ቅነሣ አደርጋለሁ ብዬ ነበር፤ አድርጌአለሁ፡፡ የኢራቅን ጦርነት አጨርሠዋለሁ ብዬ ነበር፤ ጨርሼዋለሁ፡፡ መስከረም አንድ ቀን ጥቃት ባደረሱብን ላይ አተኩሬ አሳድዳቸዋለሁ ብዬ ነበር፤ ቀድሞ ተደርጎ በማያውቅ ሁኔታ የአልቃይዳን አመራር አሳደድን፤ ኦሣማ ቢን ላደንም ተገደለ፡፡”

በመጭዎቹ አራት ዓመታት አሜሪካን ከኢኮኖሚው አዘቅት ለማውጣት እንችልባቸዋለን ሲሉ በያዟቸው ሃሣቦቻቸውም ላይ ሁለቱ ዕጩዎች በብርቱ ተሟግተዋል፡፡ የራምኒ ለባለጠጎቹ ታክስ የመቁረጥ ሃሣብ ትርፉ ኢኮኖሚውን የሚጎዳ፣ የበጀቱን ጉድለት የሚያባብስ እና በአሜሪካዊያን ላይ ጫናውን የሚያከብድ መሆኑ ነው ሲሉ ኦባማ ወቅሰዋል፡፡

ሚስተር ራምኒ ግን የኦባማን ክስ አልተቀበሉም፡፡ እንዲያውም የሥራ ፈጠራን ዕድገት የሚያመጣውና የበጀቱንም ክፍተት የሚያጠብበው የእርሣቸው የታክስ ዕቅድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡



ኢሚግሬሽንን በተመለከተ ራምኒ በሕገወጥ መንገድ ወደአሜሪካ ለገቡ ምህረት እንደማይሰጡ አስታውቀዋል፡፡ የሕጋዊው ኢሚግሬሽን ሥርዓት ወደአሜሪካ መግባትና ለመኖር የሚፈልጉ ጠበቃ ሣያስፈልጋቸው ፍቃድ የሚያገኙበት ዕድል ችሎታ እንዲኖራቸው የሚፈቅድ እንዲሆንና የሠለጠኑ ሠራተኞች ይበልጥ ቋሚ የመኖሪያ ፍቃድ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲኖር ሆኖ እንዲሻሻል እንደሚሠሩ ራምኒ አመልክተዋል፡፡

ወደ አሜሪካ በሕጋዊ መንገድ ለመግባትና ለመኖር ለሚፈልጉ የሚመች እንዲሆን የኢሚግሬሽን ሥርዓቱን ለማሻሻል ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ ማድረጋቸውን ፕሬዚዳንት ኦባማ ገልፀዋል፡፡ ለዓመታት አሜሪካ ውስጥ እየተማሩ ያሉ ወይም ቤተሰቦቻቸውን ለመመገብ ሲሉ አሜሪካ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን የማሣደድ ፍላጎት እንደሌላቸውም ተናግረዋል፡፡

ሊብያ ውስጥ የተፈፀመውን ጥቃት በተመለከተ “የተፈፀመው የሽብር ጥቃት እንደነበረ ለአሜሪካዊያን ለመንገር ሁለት ሣምንት ፈጀባቸው” ሲሉ ራምኒ ፕሬዚዳንቱን ወቅሰው “በዚያ ጥቃት ላይ ከማተኮር ይልቅ በምረጡኝ ዘመቻቸው መቀጠልን መረጡ” ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በሰጡት መልስ ጥቃቱን የሽብር ጥቃት እንደነበረ የተናገሩት በማግሥቱ እንደነበረ አስታውሰው ሊብያ ውስጥ የተፈፀመውን አመፃ ጉዳይ በመንግሥታቸው ውስጥ ለፖለቲካ ጥቅምና አሜሪካዊያንን ለማሣሣት እንደተፈፀመ አድርጎ ማውራት የሚያስቀይም መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ባለፈው የመጀመሪያ ዙር ክርክራቸው የሚስተር ራምኒ አቀራረብ እና አፈፃፀም ከፕሬዚዳንቱ የተሻለና ጠንካራም እንደነበረ ተንታኞችና የሕዝብ አስተያየት ያሣዩ ሲሆን ከክርክሩ ብኋላ በብዙዎቹ "ዋዣቂ" የሚባሉ፤ የምርጫውን ሂደትና ዕጣ ፈንታውን በሚወስኑ ግዛቶች ውስጥ ባሉ መራጮች ዘንድ ቀደም ሲል ሲመሩ የነበሩት ፕሬዚዳንት ኦባማ በተወሰኑ ነጥቦች እየተመሩ መምጣታቸውን የሚያሣዩ የሕዝብ አስተያየት ቅኝት አመላካቾች ወጥተዋል፡፡



በማክሰኞው ሁለተኛ ዙር ክርክር በተከታታዮች ዘንድ በተካሄደ የመጀመሪያ ደረጃ ቀጥተኛ ቅኝት ፕሬዚዳንቱ ማሸነፋቸውን የሚጠቁሙ ቁጥሮች ወጥተዋል፡፡

በፍሎሪዳ ግዛት ቦካ ሬተን በሚገኘው ሊን ዩኒቨርሲቲ የፊታችን ሰኞ፣ ጥቅምት 12 ቀን 2005 ዓ.ም የሚካሄደው ሦስተኛውና የመጨረሻው ዙር የዕጩ ፕሬዚዳንቶቹ ክርክር የሚያተኩረው በውጭ ጉዳዮች ላይ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

ክርክሩን የመራችው የሲኤንኤን ጋዜጠኛ ካንዲ ክሮውሊ