የሰሜን ኮሪያ ሰላዮች የቪኦኤ ጋዜጠኞችን በመምሰል መረጃ ለመመንተፍ ሞከሩ

  • ቪኦኤ ዜና

የአሜሪካ ድምፅ፣ ዋሺንግተን ዲሲ

የሰሜን ኮሪያ የመረጃ ገጸ ድር ላይ ጠላፊዎች፣ የአሜሪካ የኒውክሌር ደኅንነት እና የጦር መሣሪያ ፖሊሲ ባለሞያዎችን፣ የቪኦኤ ጋዜጠኞች በመምሰል መረጃ ለመመንተፍ፣ የኢሜይል ልውውጥ ማድረጋቸውን፣ አንድ የመረጃ ደኅንነት ጥናት ተቋም አስታወቀ፡፡

የመረጃ መረብ ጠላፊዎቹ ባለሥልጣናት፣ በሰሜን ኮሪያ ላይ ያላቸውን አቋም ለማግኘት መሞከራቸውን፣ ማንዲያንት የተሰኘው የመረጃ ደኅንነት ተቋም ለቪኦኤ አስታውቋል።

“ኤፒቲ 43” ወይም “ኪምሱኪ” እንዲሁም “ታሊየም” በመባል የሚታወቁት የሰሜን ኮሪያ የመረጃ መረብ ላይ ሰላዮች ጋዜጠኛ በመምሰል በአሜሪካና ደቡብ ኮሪያ የሚገኙ መንግስታዊ ተቋማትን፣ ምሁራንን እንዲሁም በጥናት ተቋሞች ውስጥ የሚሠሩ ተመራማሪዎችን ኢላማ አድርገዋል ሲሉ የጉግል ኩባንያ ተቀጥላ የሆነው የማንዲያት ከፍተኛ አጥኚ የሆኑት ጌሪ ፍሪያስ ለቪኦኤ ተናግረዋል፡፡

ሰላዮቹ በአምስት የሚዲያ ተቋማት የሚሠሩ ሰባት ጋዜጠኞችን ለመምሰል ሙከራ አድርገዋል ተብሏል፡፡

ጋዜጠኞቻችንን መስለው የሚቀርቡ መጥፎ ዓላማ ያላቸው ቡድኖች እንዳሉ እናውቃለን፣ የኑክሌር ጉዳይን ጨምሮ ሌሎችንም መረጃዎች ከሦስተኛ ወገኖች ለማግኘት እንደሚሞክሩ በሚገባ እናውቃለን፣ አስመስለው የሚቀርቡ ቡድኖችን በተመለከተ ለምንጮቻችን ተገቢውን ግንዛቤ እናስጨብጣለን”

የኮሪያን ባህረ ሰላጤ በተመለከተ አንዳንድ መገለጽ የሌለባቸውን መረጃዎች ሰላዮቹ ማግኘት መቻላቸውንና፣ ኢላማ የተደረጉት ግለሠቦች፣ ኑክሌርንና የሚሳዬል ሙከራዎችን ጨምሮ የሰሜን ኮሪያን እንቅስቃሴ በተመለከተ የምዕራቡ ዓለም ያለውን ስሜት በተመለከተ ሰላዮቹ መረጃዎችን ማግኘት መቻላቸውን ፍሪያስ ለቪኦኤ ተናግረዋል፡፡

“ጋዜጠኞቻችንን መስለው የሚቀርቡ መጥፎ ዓላማ ያላቸው ቡድኖች እንዳሉ እናውቃለን፣ የኑክሌር ጉዳይን ጨምሮ ሌሎችንም መረጃዎች ከሦስተኛ ወገኖች ለማግኘት እንደሚሞክሩ በሚገባ እናውቃለን፣ አስመስለው የሚቀርቡ ቡድኖችን በተመለከተ ለምንጮቻችን ተገቢውን ግንዛቤ እናስጨብጣለን” ብለዋል የቪኦኤው ቃል አቀባይ ኒጌል ጊብስ፡፡