በዚህ ዓመት 12 ሺህ ደቡብ ሱዳናዊያን ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል መባሉን ዩኤንኤችሲአር አስተባበለ

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር





Your browser doesn’t support HTML5

በዚህ ዓመት 12 ሺህ ደቡብ ሱዳናዊያን ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል መባሉን ዩኤንኤችሲአር አስተባበለ


በያዝነው የአውሮፓዊያን ዓመት ከደቡብ ሱዳን እየተሰደዱ ወደ አጎራባች ሃገሮች የገቡት ደቡብ ሱዳናዊያን ቁጥር ከ19 ሺህ እንደሚበልጥ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን እየጠቀሱ ቢዘግቡም የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር የኢትዮጵያ ቢሮ የተጠቀሰው ቁጥር ትክክል አለመሆኑን አስታውቋል፡፡

ዘገባውን የመንግሥታቱን ድርጅት ጠቅሰው ያሠራጩት ራዲዮ ባኺታ ኤፍ ኤም የሚባል የደቡብ ሱዳን ራዲዮ ጣቢያ፣ ሮይተርስ እና አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ናቸው፡፡

በዚህ ዓመት ማለትም ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ከደቡብ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የፈለሰው ስደተኛ 12 ሺህ እንደደርስና ከሚያዝያ 29 እስከ ግንቦት 16/2005 ዓ.ም ባሉት ሁለት ሣምንታት ተኩል ጊዜ ውስጥ አራት ሺህ ስደተኛ መግባቱን ዘገባዎቹ ጠቁመዋል፡፡

ስለሁኔታውና ስለዘገባዎቹም ለቪኦኤ መግለጫ የሰጡት የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር የኢትዮጵያ ቢሮ ቃልአቀባይ አቶ ክሱት ገብረእግዚአብሔር ከደቡብ ሱዳን ወደ 15 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች ወደኢትዮጵያ የገቡት ባለፈው የአውሮፓዊያን ዓመት መሁኑን ጠቁመው በዚህ ዓመት ደቡብ ሱዳን ጆንግሌይ ክፍለሃገር ውስጥ ግጭት ከተነሣ ወዲህ የገቡት ሰዎች ቁጥር ከስድስት መቶ እንደማይበልጥ አቶ ክሱት አመልክተዋል፡፡

በደቡብ ሱዳን ጆንግሌይ ግዛት ውስጥ ይህ በቅርቡ ተነሣ የተባለ ግጭትና አለመረጋጋቱ የሃገሪቱ መንግሥት በአባባቢው የጀመረውን የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ማስተጓጎሉ ተነግሯል፡፡

ለተጨማሪና ዝርዝር የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡