ሥልጣን የጨበጡ ሁሉ የእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ የእውነተኛ ነፃነት ግንባታ ከባድ እንደሆነ ተገንዝበው በተቃውሞ ላይ ማሣደድና አፈና እንዳያካሂዱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አሳሰቡ፡፡
Your browser doesn’t support HTML5
Your browser doesn’t support HTML5
ሚስተር ኦባማ ዛሬ ኒው ዮርክ ላይ ለተከፈተው ንግግር ያደርጋሉ ተብለው የሚጠበቁትን የኢትዮጵያውን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝን ጨምሮ ከ120 በላይ ሃገሮች መሪዎች በተገኙበት 67ተኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ባደረጉት ንግግር፣ የዓለም መሪዎች ዓመፅ፣ ሁከትና ፅንፈኝነትን እንዲያወግዙና በተግባር እንዲቆሙ ጠይቀዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ንግግራቸውን የጀመሩት በቅርቡ ሊብያ ውስጥ የተገደሉ አምባሣደራቸውን ክሪስቶፈር ስቲቨንስን በመዘከር ነበር፡፡
“ይህንን ታሪክ የምነግራችሁ - አሉ ፕሬዚዳንት ኦባማ ለታዳሚዎቹ - ክሪስቶፈር ስቲቨንስ አሜሪካ ያሏትን ምርጥ ነገሮች የሚወክል በመሆኑ ነው፡፡ - ትሁት ሆኖ አገልግሏል፤ ደግሞም ሰዎች የራሣውን ዕጣ ፈንታ እራሣቸው የሚወስኑበት ነፃነት እንዲኖራቸው፣ በነፃነት፣ በክብር፣ በፍትሕና የዕድሎች ተጠቃሚ ሆነው እንዲኖሩ ለሚያበቁ በርካታ መርሆች ኖሯል፡፡”
በቅርቡ የወጣውና የእሥልምናን ክብር ይነካል የተባለውን ቪድዮ ኦባማ “ኋላቀር” እና ቀፋፊ” ወይም “አስጠሊታ” ብለው የጠሩት ሲሆን መንግሥታቸው “…ከቪድዮው ጋር አንዳችም ግንኙነት እንደሌለው ግልፅ አድርጌአለሁ፤ በውስጡ የሰፈረው መልዕክትም የጋራ ሰብዕናችንን በሚያከብብሩ ሁሉ መወገዝ አለበት ብለን እናምናለን” ብለዋል፡፡
ዴሞክራሲ ድምፅ በመሰጠቱ፣ ምርጫ በመኖሩ ብቻ የሚገለፅ አለመሆኑን ያስታወሱት ኦባማ “በእውነተኛው ዴሞክራሲ ዜጎች ወደ ወኅኒ መጣል የለባቸውም፤ ልማትም ያለሙስና ሊበረታታ ይገባዋል፤ የሕግ የበላይነት ይሰፍን ዘንድም ግድ ነው” ብለዋል፡፡ “ዕውነተኛ ዲሞክራሲን፣ ዕውነተኛ ነፃነትን ማስፈን ከባድ ሥራ ነው፡፡ ሥልጣን የጨበጡ ሁሉ ተቃውሞን የማሣደድን የውስጣቸውን ግፊትና ፈተና መቋቋም መቻል አለባቸው፡፡
የየሃገሩ የምጣኔ ሃብት ሁኔታ በሚዳከምበት ጊዜ መንግሥታት ከባዱንና ፈታኙን ለውጥ በራሣቸው ዘንድ ከማድረግ ይልቅ ሕዝቦቻቸውን በሃገር ውስጥም ይሁን በውጭ በሚያመላክቱት የፈጠራ ጠላት ላይ ማነሣሣት ይዳዳቸዋል፡፡” ብለዋል የአሜሪካው ፕሬዚዳንት አክለው፡፡
ሕፃናትን ማስተማር፣ ዕድሎችን መፍጠርና ማስፋት፣ ሰብዓዊ መብቶችን መጠበቅ፣ የዴሞክራሲ ቃሎችን መንከባከብ ብዙ ፈተናዎች ያሉባቸው ቢሆንም አሜሪካ ግን ለዚያ እንደምትቆም፤ በዓለም ላይ ፊቷን እንደማታዞር አረጋግጠዋል፡፡
ዘገባውን ያዳምጡ፡፡