ቱርክ ከዩክሬን ጋር የመከላከያ ኢንደስትሪዋን ልታጠናከር ነው

  • ቪኦኤ ዜና

የቱርክ ፕሬዚዳንት ጣይብ ኤርዳጎን እና የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ

ትናንት ሀሙስ ዩክሬንን የጎበኙት የቱርክ ፕሬዚዳንት ጣይብ ኤርዳጎን፣ ሁለቱ አገሮች የመከላከያ ኢንደስትሪያቸውን፣ የበለጠ በጋራ የሚያሳድጉበት እድል መኖሩን የተገነዘቡበት መሆኑን አስታወቁ፡፡

ከዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ጋር የተገናኙት ኤርዶጋን ወደ ዩክሬን ያመሩት ሩሲያ በዩክሬን ፍጥጫ በከረረበት ወቅት ነው፡፡

ሁለቱ አገሮች የጋራ የመከላከያ ኢንደስትሪያዎችን ማስፋፋት የጉብኘቱ ዋነኛ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቱርክ ተዋጊ ድሮኖችን ዩክሬን ውስጥ ማምረትና ማስፋፋት እንዲሁም የድሮን አብራሪዎችን ማሰልጠን የምትፈልግ መሆኑ ተገልጿል፡ በአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ተመራማሪ የሆኑት ስሊ ኣያዲንታስባስ ቱርክ በዚህ ግንኙነት የበለጠ ተጠቃሚ ትሆናለች በማለት እንዲህ ይላሉ

“ቱርክ ለዩክሬን ድሮን ትሸጣለች፡፡ እውነት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ፑትንን የሚያስቆጣ መሆኑን እያወቀች ሁሉ ታደርገዋለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከዩክሬን ስለጦር መሣሪያዎች አሰራር በተለይ ስለሞተር ልምድ ትወስዳለች፡፡ በሶቭየት ህብረት ውስጥ የጦር መሳሪያ ማምረቻ ማዕከል ከነበረቸው ዩክሬን ቱርክ ጉድለቷን የምታሟላበትና የምታገኘው ብዙ እውቀት አለ፡፡”

የመካለከያ ተንታኝ የሆኑት አርዳ ሚቨሉቶግሉ ቱርክ ከራሷ በተጨማሪ ስለተዋጊ ጀቶች ሞተር አሰራር የሌሎችን እውቀትና ቴክኖሎጂ የምትፈግልበት ምክንያት መኖሩን እንደሚከተለው ይገልጻሉ፡፡

“ቱርክ የጦር መሳሪያ ማመረቻዎችን ዓይነት ማብዛት ትፈልጋለች፡፡ ከዚህ ቀደም የቱርክ ጦር መሳሪያ አምራቾች ይተማመኑ የነበረው በዩናይትድ ስቴትስ እና አውሮፓውያን አምራቾች ነበር፡፡ አሁን በተፈጠረው የፖለቲካና የማዕቀብ ጣጣ ከምዕራብ አገሮች የምታገኛቸው የቴክኖሎጂ ግብአቶች እጥረት እየገጠማት ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ አንጻር ከም ዕራባውያን አገሮች ይልቅ ዩክሬን ትልቅ አማራጭ ትሆናለች፡፡”

የቱርክ ከዩክሬን ጋር በጥብቅ መቆራኘትን ሩሲያ አትደግፈውም፡፡ ባላፈው ጥቅምት ወር ዩክሬን በሩሲያ በሚደገፉ አማጽያን ላይ ቱርክ ሠራሽ ድሮኑን መጠቀሟን በጥብቅ ኮንናለች፡፡ ቱርክ ከዩክሬን ጋር በምትፈጠረው ወዳጅነት ከሩሲያ የሚመጣውን ዋጋ ለመከፈል የተዘጋጅቸ መሆኑም ተልክቷል፡፡