በትግራይ ክልል የተደቀነውን የከበደ ረሃብ አደጋ ለመከላከል እና የሚፈጸሙ የጭካኔ አድራጎቶች እንዲገቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአፍሪካ ህብረት በፍጥነት መንቀሳቀስ አለባቸው ሲሉ አዛውንቶቹ"ዘ ኤልደርስ" በሚል ስም የተሰባሰቡ መሪዎች ተማጽኖ አቀረቡ።
ተሞክሮዎቻቸውን እና ተሰሚነታቸውን በዓለም ዙሪያ ሰላም፣ ፍትህ እና የሰብዓዊ መብት ከበሬታ እንዲሰፍን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚጥሩ በተለያዩ የኃላፊነት ሥራዎች ያገለገሉ መሪዎች ያቀፈው ነጻ ስብስብ ይህን ያሳሰበው ዛሬ ለንደን ላይ ባወጣው መግለጫ ነው።
በቀድሞዋ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸነር ሜሪ ሮቢንሰን ሊቀ መንበርነት የሚመራውና የኖቤል የሰላም ተሸላሚዋ የቀድሞዋ የላይቤሪያ ፕሬዚደንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍና ሌሎችንም ያካተተው ስብስብ በመግለጫው የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት እና የአፍሪካ ህብረት ለትግራይ ክልል የሰብዓዊ ረድዔት እና የሰብዓዊ መብት ቀውሶች መፍትሄ ለማምጣት በአስቸኳይ እርምጃ እንዲወስዱ እናሳስባለን፣ ቀውሱ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና ጸጥታም ላይ በግልጽ አደጋ የሚደቅን ነው ብለዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጻጻሳት ፍራንሲስ በከባድ ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ለሚገኘው በተለይ ቅርቤ አድርጌ ለምመለከተው የትግራይ ህዝብ ሁከቱ እንዲያበቃለት፥ ለህዝቡ ሁሉ የምግብ እና የጤና ድጋፍ እንዲረጋገጥ በተቻለም ፍጥነት ማኅበራዊ መግባባት ይሰፍን ዘንድ አብረን ጸሎት እናድርግ ሲሉ ትናንት ዕሁድ በትዊተር ገጻቸው ተማጽነዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከትናንት በስተያ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ባስተላለፉት የቪድዮ መልዕክት መንግሥታቸው ለትግራይ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አብራርተው “ነገሮችን ወደ ውስብስብ ሁኔታ የሚቀይር ያልተገባ ተፅዕኖ ኢትዮጵያ ላይ ማድረግ ችግሮችን ያባብሳል እንጂ መፍትኄ አያስገኝም” ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም “ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን ሰብዓዊ እርዳታ ለማሻሻል ማኅበራዊ ግንኙንቶችን ለማጠናከርና መሠረታዊ አገልግሎቶቻቸው ወደነባር ይዞታቸው እንዲመለሱ ከአጋር አካላት ጋር ለመሥራት ዝግጁ ነች፤ በዚህ ወሳኝ ጊዜ ኢትዮጵያ የምትሻው የወዳጆችንና የአጋሮችን ድጋፍ እንጂ ችግሩን የበለጠ ውስብስብ የሚያደርግ ጫና አይደለም ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ሣምንት ውስጥ ባወጣው መግለጫም “የትግራይ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ለከፋ ረሃብ መጋለጣቸውን የሚገልፁ መግለጫዎች መሬት ላይ ያለውን እውነታ አያሳዩም” ሲል አሳስቧል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እና የአደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በሳምንቱ አጋማሽ ለጋዜጠኞች በሰጧቸው መግለጫዎች በአካባቢው መታረስ ከሚችለው መሬት 70 ከመቶው ለእርሻ ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰው “ይህ ደግሞ የከፋ ረሃብን ያስቀራል” ብለዋል።
በመጀመሪያው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ከአራት ሚሊየን በላይ ሰው መድረስ መቻሉን ባለሥልጣናቱ አመልክተው በሁለተኛውና በሦስተኛው ዙሮች ለ 5፡2 ሚሊየን ሰው የ135 ሚሊየን ዶላይ ግምት ያለው 798 ሺህ ሜትሪክ ቶን የዕለት ደራሽ እርዳታ በስድስት የሃገርና ዓለም አቀፍ የረድዔት ተቋማትና በመንግሥትም በቀጥታ መከፋፈሉን ተናግረዋል።
የሰብዓዊ መብቶችን አያያዝ አስመልክቶ ቀደም ሲል መግለጫ የሰጡት የሃገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቲዎስ ክልሉ ውስጥ የተፈፀሙ የመድፈርና ሌሎችም የወንጀል አድራጎቶችን እያጣሩ ክሦችን እየመሠረቱ መሆናቸውን አብራርተዋል።