ትግራይ ውስጥ የተካሄደውን ጦርነት ሁለተኛ ዓመት ለማሰብ ሰልፎች ተካሄዱ

Your browser doesn’t support HTML5

/የዚህ ዘገባ ርዕስ ከሰልፉ ዓላማ ጋር ለማጣጣም ተቀይሯል። ቀደም ሲል የተቀመጠው ርዕስ በስህተት የወጣ በመሆኑ ይቅርታ እንጠይቃለን።/

ትግራይ ውስጥ ጦርነት የተጀመረበትን ሁለተኛ ዓመት ለመዘከር ባለፈው ሣምንት የመጨረሻ ቀናትና ሰኞ ተካሂደዋል።

ሰልፈኞቹ “#TIGRAYGENOCIDE” በሚል የእንግሊዝኛ መሪ ቃል ለአራት ቀናት የጠሯቸውን ሰልፎች በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች ውስጥ ያካሄዱ ሲሆን ዋሺንግተን ዲሲ እና የዋሺንግተን ስቴት ከተማ ሲአትል ውስጥ ዋና አውራ መንገዶችን ዘግተዋል።

አዘጋጆቹ ሰልፎቹን በተመሣሣይ መንገድ ለማካሄድ የወሰኑት በትግራይ ህዝብ ላይ እየደረሰ ነው ላሉት ሞት፣ የበረታ እንግልትና መከራ ለመድረስ የሚያስችል ትኩረት ለመሳብ መሆኑን ለአሜሪካ ድምፅ ገልፀዋል።

በሰልፎቹና በጥያቄዎቹ ላይ በአሜሪካ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ የተሰማ መልክዕክት ወይም ምላሽ የለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ፀብ ፈጥኖ እንዲቆምና የህወሃት ተዋጊዎች ትጥቅ እንዲያወርዱ፣ እርዳታ ለተረጂው ህዝብ ያለገደብ እንዲደርስና መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ፌደራሉ መንግሥትና የህወሃት መሪዎች ባለፈው ሣምንት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ መስማማታቸውና መፈራረማቸው ይታወሳል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነርና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፈው ዓመት ባወጡት የምርመራ ሪፖርት በሰብዕና ላይ የተፈፀሙና የጦር ወንጀል ተብለው ሊጠቀሱ የሚችሉ ጥፋቶች በሁሉም ወገኖች መፈፀማቸውን ገልፀው ‘ዘር ማጥፋት ተካሂዷል ለማለት የሚያስችል ማስረጃ ግን አለማግኘታቸውን’ አስታውቀው ነበር።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የሰየማቸው ባለሙያዎችም በቅርቡ ባቀረቡት ሪፖርት በሁሉም ወገኖች የጦርና በሰብዕና ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች ስለመኖራቸው ቢያሳውቁም ዘር ስለማጥፋት ግን የተናገሩት ነገር የለም።

/በሰሞኑ የትግራይ ተወላጆች ሰልፎች ላይ የተጠናቀረውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ/