ዩክሬንና ሩሲያን ለማሸማገል የተጓዘው የአፍሪካ መሪዎች የሰላም ልዑክ “ታሪካዊ ነው” - ራማፎሳ

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣፣ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሰሪል ራማፎሳ

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣፣ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሰሪል ራማፎሳ

ወደ ሩሲያ እና ዩክሬን ለሰላም ሽምግልና ተጉዞ የነበረው የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ልዑክ፣ “ታሪካዊ ተጽእኖ ፈጣሪ ነበር፤” ሲሉ፣ ትላንት ከጉዞው የተመለሱት፣ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሰሪል ራማፎሳ አስታወቁ።

በሌላ በኩል፣ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ በልዑካኑ የሰላም ሐሳብ ላይ ቀዝቃዛ ውኃ ሲቸልሱበት፣ የዩክሬኑ መሪ ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ደግሞ፣ ሩሲያ ጦሯን ከአገራቸው ሳታስወጣ፣ ከሞስኮ ጋራ መደራደር የማይታሰብ ነው፤ ብለዋል።

የመሪዎች ልዑኩ፣ ባለ10 ነጥብ የሰላም ሐሳብ ማቅረቡ ሲታወቅ፣ ውጊያውን ማርገብ፥ የሀገራትን ሉዓላዊነት ማክበር፥ ያልተገደበ የውጪ የእህል ግብይት አቅርቦት፣ እንዲሁም ሴቶችንና ሕፃናትን የጦር እስረኞች ወደ አገራቸው መመለስ የሚሉት ይገኙበታል።

ክሬምሊን፣ የሰላም ሐሳቦቹን ነጥቦች ለመተግበር አስቸጋሪ እንደሚኾን ገልጿል።

“የሰላም ልዑኩ፣ የአፍሪካ መሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ከአህጉራቸው ውጪ ባሉ የሰላም ጉዳዮች ላይ የተሳተፉበት በመኾኑ፣ ታሪካዊ ነው፤” ሲሉ፣ ራማፎሳ መናገራቸውን፣ ዛሬ ሰኞ የወጣው ሳምንታዊ ዜና መጽሔት ጠቅሷል።

በመሪዎች ልዑካኑ፥ የደቡብ አፍሪካ፣ የሴኔጋል፣ የኮሞሮስ፣ የዛምቢያ ፕሬዚዳንቶችንና ከዩጋንዳ፣ ግብጽ እና ኮንጎ ብራዛቪል ደግሞ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ያቀፈ እንደነበር፣ የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።

ሩሲያም ኾነች ዩክሬን፣ “ጦርነቱን በድል እንደሚፈጽሙ በየራሳቸው ርግጠኞች በመኾናቸው፣ ሰላም ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶች ጋሬጣ እየገጠማቸው ነው፤” ሲሉ፣ ተንታኞች በመናገር ላይ ናቸው።