አዲስ የተመረጡት የሶማሊያ ፕሬዚደንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ ከኬንያ ልዑካን ጋር በተገናኙበት የሞቃዲሾ ከተማ ሆቴል ላይ አጥፍቶ ጠፊዎች ዛሬ ማለዳ ጥቃት አድርሰዋል። ከገዳዮቹ በተጨማሪ ቢያንስ ሰባት ሰዎች ሰለባ ሆነዋል።
Your browser doesn’t support HTML5
የኬንያ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳም ኦንጌሪ አገራቸዉ ፕሬዚደንት የተላከዉን የእንኩዋን ደስ ያለዎ ደብዳቤ ሲያነቡ ነበር የመጀመሪያው ፍንዳታ የተሰማው።
ከመጀመሪያው ፍንዳታ በሁዋላ ፥ ሁለተኛው አጥፍቶ ጠፊ በጃዚራ ፓላስ ሆቴል በር ፈጥኖ ወደ ውስጥ ሊገባ ሞክሮ ነበር፣ የአፍሪቃ ህብረት ባለስልጣናት እንደገለጹት ግን የታጠቀውን ቦምብ ከማፈንዳቱ በፊት የአፍሪቃ ህብረት ሃይሎች ተኩሰው ገደሉት።
በሆቴሉ ፎቆ አዳራሽ ውስጥ የነበሩት ፕሬዚደንት ሞሀሙድ ግን በተረጋጋ ሁኔታ ለኬንያ ልኡካንና ለሚከታተሉ የመገናኛ ብዙሃን አባላት ንግግር ማድረጋቸውን ቀጠሉ። እንዲህ ዓይነቱ አሁን የምንሰማው ፍንዳታ በሶማሊያ የተለመደ ቢሆንም፣ እንደሚያበቃ ጽኑ እምነት አለኝ አሉ።
ጥቂት ደቂቃዎች ዘግይቶ ከሆተሉ በስተጉዋሮ ወደ በዋና ከተማዋ የአፍሪቃ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መስሪያቤት ከሚገኙበት ቅጥር ግቢ ቅርበት ላይ ሌላ ፍንዳታ ተሰማ፣ ለጥቃቱ ነውጠኛው የሶማሊያ ቡድን አልሸባብ ሃላፈነት ወስዷል።
ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው አልሸባብ አሚሶም በሚባለው የአፍሪቃ ህብረት ሃይል ድል ድል ከተመታ ወዲህ በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ጥቃት ጥሎ የማፈግፈግ የጎሬላ ስልት ነው የሚከተለው። አዲስ የተመረጡት የሶማሊያ ፕሬዚደንት ሃሳን ሞሃመድ የጸጥታ ቁጥጥር የአስተዳደራቸው ዋና ትኩረት እንደሚሆን ተናግረዋል።
”ሶማሊያ ሰላም እንዲሰፍንባት ከጎሬበቶችዋና ከተቀረውም ዓለም ጋር በሰላም እንድትኖር ጥረት እያደረግን ነው። ጸጥታን ማስፈን ዋናው ዓላማችን ነው፣ አንደኛው ሁለተኛው ሶስተኛው ዓላማችን ጸጥታን ማስከበር ነው” ብለዋል አዲሱ ፕሬዚዳንት።
ለዘብተኛ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸውና የስራ ልምዳቸው በትምህርት ተቃማት ዙሪያ የሆነው ሚስተርማህሙድ ባለፈው ሰኞ በከፍተኛ የህዝብ ድምጽ ለሶማሊያ ፕሬዚደንትነት መመረጣቸው ይታወቃል።
ሪፖርቱን ያዳምጡ።