ፕሮፌሰር ሚንጋ ነጋሽ የዛሬ ሃያ አምስት ዓመት ወደ ዚምባብዌ ለሥራ ሲሄዱ ሮበርት ሙጋቤ የተከበሩ የአፍሪካ መሪና ምሁር እንደነበሩና የሃገሪቱም ምጣኔ ኃብት በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኝ እንደነበረ ገልፀዋል።
በወቅቱ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ እርሣቸው ያስተምሩበት ወደነበረበት የዚምባብዌ ዩኒቨርሲቲ ጎራ እያሉ ከምሁራኑና ከተማሪዎች ጋርም ይወያዩ እንደነበረ አመልክተዋል።
በሾና ጎሣ አባላት በተመሠረተው በእርሣቸው ፓርቲ ዛኑ እና ተቀናቃኛቸው በነበሩት የንዴቤሌ ጎሣው ጃሽዋ ንኮሞ ዛፑ መካከል ይነሱ የነበሩ ግጭቶች በእርቅ መፈታታቸውንና ዛኑ ፒኤፍ መንበረ ሥልጣኑን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩንም ፕሮፌሰር ሚንጋ አመልክተው ዓመታት እየተቆጠሩ በሄዱ መጠንና ሙጋቤ የመጀመሪያ ባለቤታቸው ከሞቱባቸውና አሁን አብረዋቸው ያሉትን ግሬስን ካገቡ በኋላ ነገሮች እየተለወጡ መምጣታቸውን አስታውሰዋል።
በተለይ ሙጋቤ በአብዛኛው በነጮች ተይዞ የነበረውን የሃገሪቱን መሬት ነጥቀው ለጥቁሮች ለማከፋፈል የሄዱበት መንገድ በተለይ ከእንግሊዝ ጋር እንዳቃቃራቸውና ማዕቀቦችም እንዲጣሉባቸው ምክንያት መሆኑን የጠቆሙት ፕሮፌሰር ሚንጋ ይኖሩና ይሠሩባት ከነበረችው ደቡብ አፍሪካ ወደ ሃራሬ ከአሥራ ሁለት ዓመታት በኋላ ሲመለሱ ኑሮው እጅግ ተወድዶ፣ የዚምባብዌ ዶላር በእጅጉ ገሽቦና ዋጋ አጥቶ እንዳገኙት ገልፀዋል።
ገዥው ፓርቲያቸው በተቃዋሚው የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ንቅናቄ አባላት ላይም የማሳደድ ዘመቻ ማካሄዱን፣ ግሬስን ምክትል ፕሬዚዳንት የማድረግ ፍላጎታቸውም የቀድሞውን ምክትላቸውን ኤመርሰን ምናንጋግዋን ለማባረር እንዳደረሳቸው አመልክተዋል።
ኤመርሰን ምናንጋግዋ በጦሩ ተደግፈው ፕሬዚዳንት መሆናቸው በሃገሪቱ ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች ምናልባት እንዲነሱላት ዕድል ሊሰጥ እንደሚችልና የምጣኔ ኃብት መሻሻል ሊኖር እንደሚችል ያላቸውን ግምት ጠቁመው ገዥው ፓርቲ ግን ያው ዛኑ-ፒኤፍ በመሆኑ ሥር ነቀል የሆነ የፖለቲካ መሻሻል ይኖራል ብለው እንደማይጠብቁ ተናግረዋል።
ከፕሮፌሰር ሚንጋ ነጋሽ ጋር ያደረግነውን ቃለ-ምልልስ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5