እጅግ የተካረረውና ተጧጡፎ የሰነበተው እንዲሁም ረዘም ላለ ጊዜ የተካሄደው የአሜሪካ አጠቃላይ ምርጫ ትናንት ተካሂዷል፤ የአሜሪካ ሕዝብ ለነባሩ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በአብላጫ ድምፁና በምርጫ ውክልናም በተጨማሪ አራት ዓመታት የሁለተኛ ዘመን የዋይት ኃውስ ዕድሜ ቸሯቸዋል፡፡
Your browser doesn’t support HTML5
ለዩናይትድ ስቴትስ ዴሞክራቲክ ፓርቲ የትናንትናው ምሽት በእጅጉ የደመቀና የከበረ ነበር፡፡
የሪፐብሊካን ፓርቲው ብሔራዊ ኮሚቴ ያዘጋጀው ፕሮግራም መጀመሪያው ላይ በእጅጉ የተነሣሣ፣ በማሸነፍ ተስፋና ስሜት የተሞላ የነበረ ቢሆንም ወደ ኋላ ግን በፀጥታ ተውጧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የዩናይትድ ስቴትሷ ዋና ከተማ የዋሽንግተን ዲሲ ብዙዎቹ ጎዳናዎችና የዋይት ኃውስ ቤተመንግሥት አካባቢ በድል ጭፈራና በሆታ የተሞሉና የደመቁ ሆነው ሌሊቱን አሣልፈዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ዳግም እንዲመረጡ ድምፃችንን መስጠት ብቻ ሳይሆን በተለያየ መልክ ያቅማችንን አስተዋጽዖም አበርክተናል ያሉ ብዛት ያላቸው ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ውጤቱንም ባንድነት ለመስማት አርሊንግተን ቨርጂንያ በሚገኘው ዳማ ምግብ ቤት ተሰባስበው አምሽተዋል።
የዳማ ምግብ ቤት ሠራተኞችና ደንበኞቻቸው ከአራት ዓመት በፊትም ኦባማን ለማስመረጥና ውጤቱን በጋራ ለመከታተል ተመሣሣይ ፕሮግራም አዘጋጅተው እንደነበር ይታወሣል፡፡
ሰሎሞን አባተ የዴሞክራቲክ ፓርቲውን ብሔራዊ ኮሚቴ፣ ሄኖክ ሰማእግዜር የሪፐብሊካን ፓርቲውን ዝግጅቶች እና የከተማይቱን ድኅረ ምርጫ ፈንጠዝያ፣ እንዲሁም ሰሎሞን ክፍሌ የዳማ ሬስቶራንትን ሥነ-ሥርዓት ተከታትለዋል፡፡
ዝርዝሩን ያዳምጡ፡፡