በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከሦስት ሺሕ በላይ መምህራንና ተማሪዎች መሞታቸው ተገለጸ

Your browser doesn’t support HTML5

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ በትግራይ ክልል ውስጥ፣ ከ3ሺሕ800 በላይ መምህራንና ተማሪዎች ሕይወት ማለፉን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ፡፡ ተቋሙ፣ ጦርነቱ በክልሉ ስላደረሰው ጉዳት በአካሔደው የዳሰሳ ጥናት፣ በትምህርት ሥርዐቱም ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን አመልክቷል፡፡

የጉዳት መጠኑ፣ በቅርቡ በተጀመረው የመማር ማስተማር ሒደት ላይ ከፍተኛ እክል እንደፈጠረ በተቋሙ የተገለጸ ሲኾን፣ የክልሉ የትምህርት ቢሮ በበኩሉ፣ የሚመለከታቸው የፌዴራል አካላት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ አለማድረጋቸውን በመጥቀስ ወቀሳ አሰምቷል፡፡

የተቋሙ ዋና እንባ ጠባቂ ዶ/ር እንዳለ ኃይሌ፣ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፥ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከማይቆጣጠራቸው 26 ወረዳዎች ውጪ ባሉት የክልሉ አካባቢዎች፣ እስከ ወርኀ ነሐሴ 2013 ዓ.ም. ድረስ ብቻ ያለውን የጦርነት ጉዳት ያካተተ ጥናት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በጦርነቱ፥ በሺሕዎች የሚቆጠሩ መምህራንና ተማሪዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ መረጋገጡን የጠቀሱት ዋና እንባ ጠባቂው፣ ውድመቱ፥ በመማር ማስተማር ሒደቱም ላይ፣ አሉታዊ ተጽእኖ መፍጠሩን አመልክተዋል፡፡

የትግራይ ትምህርት ቢሮ ሓላፊ ዶር. ኪሮስ ጉዑሽ በበኩላቸው፣ በጥናቱ ከተጠቀሰው ከነሐሴ 2013 ዓ.ም. በኋላም፣ በክልሉ በተካሔደ ጦርነት፣ ብዙ ውድመት መድረሱን ተናግረዋል፡፡

የተቋሙ ጥናት እንደሚያሳየው፣ እስከ ነሐሴ 2013 ዓ.ም. ድረስ፣ 88 ከመቶ የሚኾኑት የመማሪያ ክፍሎች በሙሉ እና በከፊል ተጎድተዋል፤ 96 ከመቶ የሚኾኑት የተማሪዎች መቀመጫ ዴስኮች ወድመዋል፤ 95ነጥብ8 ከመቶ የመማሪያ ጥቁር ሰሌዳዎችም አልተገኙም፡፡

ይኸው የጉዳት መጠን፣ በቅርቡ በተጀመረው የመማር ማስተማር ሒደት ላይ እክል እንደፈጠረ፣ ዋና እንባ ጠባቂው ዶ/ር እንዳለ ኃይሌ ያስረዳሉ፡፡

በትግራይ ክልል የትምህርት ዘርፍ የደረሰው ውድመት፣ ግዙፍ እንደኾነ የሚናገሩት የቢሮ ሓላፊው ዶር. ኪሮስ ጉዑሽ፣ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ “የተማሪዎች አፈጻጸም ዝቅተኛ ነው፤ የትምህርት ጥራት ወረደ፤ ሲባል እንሰማለን፤ በትግራይ ግን ይህን መጠየቅ ቅንጦት ነው፤” ብለዋል፡፡

የሚመለከታቸው የፌዴራል አካላት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ትምህርት መጀመራችንን አይተው ግብአት በማቅረብ ያግዙናል ብለን ተስፋ ብናደርግም፣ እስከ አሁን ድረስ፣ በተግባር ያየነው ነገር የለም፤ ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ ዶር. እንዳለም፣ ይህን ችግር ለመፍታት፣ የሁሉም አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡን የትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ዓመለ ወርቅ ሕዝቅኤል፣ መሥሪያ ቤታቸው፥ ወደ ትግራይ ክልል የትምህርት ቁሳቁስ ለመላክ በዝግጅት ላይ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡

መነሻውን በትግራይ ክልል በአደረገው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት፣ በክልሉ የትምህርት ዘርፍ ላይ ምን ያህል አጠቃላይ ውድመት እንደደረሰ፣ እየተጠና እንደኾነና በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ፣ ዶር. ኪሮስ ጉዑሽ አክለው ገልጸዋል፡፡