የአሜሪካ ፕሬዚዳንት እና የኢራን ፕሬዚዳንት ተነጋገሩ

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ /የስልክ ውይይት ከኦቫል ኦፊስ - ዋይት ሃውስ ቤተመንግሥት/ /ፎቶ - ፋይል/

ከአራን ፕሬዚዳንት ሃሰን ሩሃኒ ጋር ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት በስልክ መነጋገራቸውን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አስታወቁ፡፡



የአራን ፕሬዚዳንት ሃሰን ሩሃኒ /ፎቶ - ፋይል/


ከአራን ፕሬዚዳንት ሃሰን ሩሃኒ ጋር ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት በስልክ መነጋገራቸውን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አስታወቁ፡፡

የሁለቱ ሃገሮች ፕሬዚዳንቶች በምንም ጉዳይ ላይ ይሁን እንዲህ ሲነጋገሩ ላለፉት 34 ዓመታት ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በዋይት ሃውስ ቤተመንግሥት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

መሪዎቹ ገንቢ ውይይት ማድረጋቸውን ፕሬዚዳንት ኦባማ ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ ሃገሮች በኢራን የኒኩሌር መርኃግብር ላይ አጠቃላይ መፍትኄ ማግኘት እንደሚችሉ ያላቸውን እምነት የገለፁት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዛሬ ከኢራን አቻቸው ጋር ያደረጉት የስልክ ውይይት “ወደፊት መንቀሣቀስ እንደሚቻል ያሳያል” ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ /ፎቶ - ፋይል/


ዩናይትድ ስቴትስ እንዲህ ዓይነቱን ግንኙነት እሥራኤልን ጨምራ ከወዳጆቿ ሁሉ ጋር እንደምታስተባብር አስታውቀዋል፡፡

የኢራኑ ፕሬዚዳንት ሃሰን ሩሃኒ ዛሬ ማለዳ ላይ ሲናገሩ “በኢራን የኒኩሌር መርኃግብር ላይ ከኃያላኑ መንግሥታት ጋር የተጀመረው ንግግር በቅርቡ ፍሬ ያፈራል የሚል ተስፋ አለኝ” ብለው ነበር፡፡

ሩሃኒ ኒው ዮርክ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ሚስተር ኦባማ ያሰሙት አዲስ የንግግር ቃና በዚህ የኒኩሌር ጉዳይ ላይ ፈጣን መፍትኄ ማግኘት እንደሚቻል ብርቱ እምነትን በውስጣቸው ማሳደሩን አመልክተዋል፡፡

ሰኔ ውስጥ በተካሄደው ምርጫ እርሳቸው ወደ መንበረ-ሥልጣኑ መውጣታቸው በኢራን እና በምዕራቡ መካከል ለተሻለ ግንኙነት መንገድ እንዲጠረግ ያስቻለ መሆኑን ሩሃኒ ገልፀዋል፡፡