በናይጄሪያው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ማን ያሸነፋል?

Your browser doesn’t support HTML5

በ24 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ፉክክር የሚታይበት የናይጄሪያ ፕሬዚዳናታዊ ምርጫ ተቃርቧል፡፡ በአፍሪካ ትልቁን የሕዝብ ብዛት ያላት፣ በተባባሰው የጸጥታና የምጣኔ ኃብት ቀውስ ውስጥ የምትገኘው ናይጄሪያ፣ አዲሱ ፕሬዚዳንቷን ለመምረጥ ቅዳሜ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ታመራለች፡፡

ከጥሬ ገንዘብ እና የነዳጅ እጥረቱ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ውጥረት ሰዎች ድምጻቸውን የሚሰጡበትን ሁኔታ እንደሚወስነው ተመልክቷል፡፡

በሀገሪቱ ከፍተኛው መራጭ የሚሳተፍበት መሆኑ በተነገረለት ምርጫ 93.4 ሚሊዮን ናይጄሪያውያን ለመምረጥ ተመዝግበዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከ10 ሚልዮን በላይ የሚሆኑት አዳዲስ መራጮች ሲሆኑ አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው፡፡ ይህ በመሆኑ ታዛቢዎች ይኸኛው ምርጫ ከእስከዛሬዎቹ ሁሉ የተለየ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ታዛቢዎቹ ፒተር ኦቢ የአዳዲሶቹን መራጮች ድምጽ በተሻለ ሁኔታ ሊያገኙ እንደሚችሉ ገምተዋል፡፡

ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በሁለቱ ዋና ዋና ፓርቲዎች መካከል ብቻ በተመለደበት አገር ኦቢ ሦስተኛ አማራጭ ሆነው መቅረባቸው ሥጋት መፍጠሩን ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡

የአቡጃ ነዋሪ ጄሰን ኦንዊ እንደሚሉት ኦቢ ለሥራው የተገቡ ሰው ናቸው ይላሉ፤ “ለኔ እኝህ ሰው ከምንም የጸዱ ናቸው፡፡ እኔ ላይ የምታሰሙት አንዳች ክስ ካል እስኪ ወዲህ በሉና ልመልከተው እያሉ ነው፡፡ እስከዛሬ አንድም ሰው አንድም ክስ አላመጣባቸውም፡፡ ድምጼን ለፒተር ኦቢ የምስጠው ለዚህ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

ኦቢ የኢኮኖሚ ተሀድሶ እና ለሚዛናዊ የመንግሥት ወጭ እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የሚወዳደሩት በናይጄሪያ ፖለቲካ ሥራቸውን እስከታች ከተከሉ ትላልቅ አካላት ጋር ነው፡፡

ቦላ አህመድ ቲኑቡ ፖለቲካውን በመዘወር የሚታወቁ የገዥው ፓርቲ እጩ ናቸው፡፡ የደህንነት ችግርን ለማስወገድና የተሰናባቹን የፕሬዚዳንት መሃሙዱ ቡሃሪን ፖሊሲ እንደሚቀጥሉበት ቃል ገብተዋል፡፡

የትልቁ ተቃዋሚ የሕዝቦች ዲሞክራቲክ ፓርቲ እጩ የሆኑት የቀደሞው ምክትል ፕሬዚዳንት አቲኩ አቡባከርም ሌላው ተፎካካሪ ናቸው፡፡ የሳቸው ደጋፊዎች ያላቸው የተከባተ ልምድ የተሻሉ ተመራጭ ያደርጋቸዋል ይላሉ፡፡

ናይጄሪያ እጅግ የተስፋፋውን የጸጥታ ችግር ለመቋቋምና በአፍንጫው የተደፋውን ኢኮኖሚ ለማቃናት እየታገለች ነው፡፡ ባለሞያዎች ግን በዚህ ጊዜ ያለውን የመራጮች ድምጽ የሚወስነው እሱ ብቻ አይደለም ይላሉ፡፡

የዴሞክራሲና ልማት ማዕከል ዳይሬክተር ኢዳያት ሃሰን “የነዳጅ ዘይት አምራች በሆነቸው ናይጄሪያ ያለው የነዳጅ እጥረት እና የአገሪቱ ገንዘብ ኔራ እጥረት፣አሁን በአገሪቱ ያለውን ጠቅላላ የምርጫ ሥርዓት እየቀየረው ነው፡፡” ብለዋል።

ኢዳያት አያይዘውም “ሰዎች እንዴት እንደሚመርጡ፣ ትንሿ ነገር ሳትቀር ለውጥ በምታመጣበት፣ እጅግ ተቀራራቢ ፉክክር በሚካሄደበት የምርጫው ቀን ለማየት የምንጠብቀው ነገር የተለየ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

የናይጄሪያ ማዕከላዊ ባንክ የጥሬ ገንዘብ እጥረት ያስከተለውን ችግር ለማስተካከል የገንዘብ ልውውጥ ተሃድሶ እያደረገ ነው፡፡

ብዙዎቹ እጩዎቹ ማዕከላዊ ባንኩ የገንዘብ ሽግግሩን ቀነ ገደብ እንዲያራዝም ቢጠይቁም በፕሬዚዳንቱ የሚደገፈው ባንክ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፡፡

የአቡጃ ነዋሪ የሆኑት አልዩ አቡድላሂ በጥሬ ገንዘቡ ፖሊሲ እየተቸገሩ መሆኑን ገልጸው “ከሦስት ቀናት በፊት የጥሬ ገንዘብ ለውጡ ጉዳይ በብዙ አካባቢዎች ብጥብጥ እንዲፈጠር በማድረጉ ሁለት ሰዎች ሞተዋል፡፡ እኔም እዚህ አፍንጫዬ ላይ ያለው ቁስል የዚያን ቀን የቆሰልኩት ነው፡፡” ብለዋል፡፡

በምርጫው ሂደት በብዙ አካባቢዎች የምርጫ ሠራተኞች ጥቃት እየደረሰባቸ ነው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለምርጫው እየተዘጋጁ ባሉበት ወቅት ግጭት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት መኖሩም ተመልክቷል።