የሱዳኑን ግጭት የሸሹ ፍልሰተኞች በመተማ እና በኩምሩክ እየገቡ ነው - አይኦኤም

Your browser doesn’t support HTML5

የሱዳኑን ግጭት በመሸሽ፣ የኢትዮጵያ የድንበር ከተማ - መተማ የደረሱ ኢትዮጵያውያንና የሌሎች ሀገራት ዜጎች ቁጥር፣ ከ18ሺሕ በላይ መድረሱን፣ ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(IOM) አስታውቋል።

ከመተማ በተጨማሪ በኩምሩክ በኩል ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልም፣ ከ600 በላይ ሰዎች መግባታቸውን፣ የድርጅቱ የኢትዮጵያ ቃል አቀባይ ኬ ቪራይ፣ ለአሜሪካ ድምፅ አብራርተዋል።

በየአካባቢዎቹ የሚገኙ የአስተዳደር አካላትም፣ ኢትዮጵያውያንና የልዩ ልዩ ሀገራት ዜጎች፣ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን እንደቀጠሉ አመልክተዋል።

በሱዳን፣ ወር ሊሞላው ከተቃረበው ግጭት የሸሹ የልዩ ልዩ ሀገራት ዜጎች፣ አገሪቱን እየለቀቁ፣ በምዕራብ ጎንደሯ የድንበር ከተማ መተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን መቀጠላቸውን፣ ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(IOM) አስታውቋል።

የድርጅቱ የኢትዮጵያ ቃል አቀባይ ኬ ቪራይ፣ ለአሜሪካ ድምፅ እንዳብራሩት፣ እስከ አሁን መተማ የደረሱት ኢትዮጵያውያንና የሌሎች ሀገራት ዜጎች ቁጥር ከ18ሺሕ በላይ ነው።

ይኸው ቁጥር፣ በቀጣዮቹ ወራት፥ ከ130ሺሕ በላይ ሊደርስ እንደሚችል፣ የፍልሰት ድርጅቱ ግምቱን አስቀምጧል። ከእኒኽም፣ 100ሺሕ ኢትዮጵያውያንና 30ሺሕ የሌሎች ሀገራት ዜጎች እንደኾኑ ድርጅቱ አመልክቷል፡፡

የዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅቱ ቃል አቀባይ ኬ ቪራይ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢ እስክንድር ፍሬው በሰጡት ምላሽ፣ የዚኽን ግምት መነሻ አብራርተዋል።

የቀጣዮቹ ወራት ፍልሰተኞች ቁጥር መነሻችን፣ ግጭቱን ሽሽት የሚገቡትን ሰዎች መከታተል ከጀመርንበት፣ እ.እ.አ ከሚያዝያ 21 ቀን ጀምሮ እየተመለከትን ያለነውን አካሔድ መነሻ ያደረገ ነው። በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት፣ በየቀኑ የሚገቡት ሰዎች አማካይ ቁጥር አንድ ሺሕ ነበር። በተለያዩ ቀናት ቁጥሩ ከ700 ጀምሮ፣ ከአንድ ሺሕም በላይ የደረሰበት ጊዜ ነበር።

የሱዳኑን ግጭት የሸሹ ሰዎች ወደ ኢትዮዮጵያ እየገቡ ያሉት፣ በምዕራብ ጎንደሯ የድንበር ከተማ መተማ በኩል ብቻ ሳይኾን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች፣ በቤንሻንጉል ጉምዝም በኩል መግባታቸውን፣ ኬ ቪራይ አስረድተዋል።

የፍልሰት ድርጅቱ፣ ለሱዳኑ ቀውስ እየሰጠ ያለውን ምላሽ በአሳደገበት ማሕቀፍ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልልም፣ በኩምሩክ የሚገኝ ሌላ ተጨማሪ መተላለፊያ ቦታንም እየተከታተልን ነው። እስከ አሁን በዚኽ መተላለፊያ በኩል፣ ከ600 በላይ ሰዎች መግባታቸውን መዝግበናል።

በዚያው በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ መተከል ውስጥ በሚገኝና አልምሃል በተባለ ሌላ መተላለፊያ በኩል እየገቡ ያሉ ሰዎች እንዳሉም የተወሰነ መረጃ ደርሶናል። የገቡትን ሰዎች ቁጥር ግን ገና ማረጋገጥ ይኖርብናል።

በሱዳን ድንበር አካባቢ የሚገኙ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት፣ የሱዳኑን ግጭት ሸሽተው የሚመጡ ፍልሰተኞች፣ በቂ ድጋፍ እየተደረገላቸው መኾኑን ገልጸዋል፡፡

በዐማራ ክልል፣ የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢክስ ወርቄ፣ በአሁኑ ሰዓት፣ በቀን በአማካይ አንድ ሺሕ ፍልሰተኞች፣ የሱዳንን ድንበር አቋርጠው በመተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መኾኑን ጠቅሰው፣ ከሱዳን የድንበር ከተማ ባለሥልጣናት ጋራ በመነጋገር ችግር እንዳይገጥማቸው በጋራ እየሠራን ነው፤ ብለዋል

የሱዳን ድንበር በኾነችው በገላባት በኩል፣ የሱዳን ዜግነት ያላቸው በርካታ ፍልሰተኞች መኖራቸውን ያመለከቱት አቶ ቢክስ፣ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ተሻግረው ከገቡት ፍልሰተኞች መካከል፣ እስከ አሁን በተዘጋጀው መጠለያ ጣቢያ ላይ ያረፈ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የአሶሳ ዞን አስተዳዳሪ አቶ እድሪስ መሐመድ፣ የሱዳን ድንበር አዋሳኝ በኾነችው ኩምሩክ በኩል፣ የሱዳንና የሌሎች ሀገር ዜግነት ያላቸው ፍልሰተኞች መግባታቸውንና በመጠለያ ውስጥ ኾነው አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዳለ አስታውቀዋል፡፡

በሁለቱም ሀገራት የድንበር አካባቢዎች፣ የተመድ ዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት፣ ለማረፊያነት የሚያገለግሉ መጠለያዎችን እየገነባና ሌሎችንም ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ፣ ባለሥልጣናቱ ገልጸዋል፡፡