ከ12 ሺሕ በላይ ሰዎች ከሱዳን ተሰደው ኢትዮጵያ ገብተዋል

Your browser doesn’t support HTML5

የሱዳኑን ግጭት በመሸሽ፣ እስከ አሁን ከ12 ሺሕ በላይ ሰዎች ከአገሪቱ ተሰድደው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን፣ ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(አይኦኤም) አስታወቀ፡፡

በሱዳን ያለውን ግጭት በመሸሽ፣ በየቀኑ ከ1000 በላይ ስደተኞች ድንበር ላይ ወደምትገኘው የኢትዮጵያዋ መተማ ከተማ እየገቡ መኾናቸውንም፣ የድርጅቱ የኢትዮጵያ ቃለ አቀባይ ኬ ቪራይ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ላሉ ስደተኞች፣ ልዩ ልዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ የገለጸው ድርጅቱ፣ እየጨመረ ያለውን ፍላጎት ለማሟላት፣ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እገዛ ያስፈልጋል፤ ብለዋል፡፡

ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(አይኦኤም) በአወጣው መግለጫ፣ በሱዳን ከ20 ቀናት በፊት የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ እስከ አሁን ከ12 ሺሕ በላይ ሰዎች ከአገሪቱ ተሰደው ኢትዮጵያ መግባታቸውን አስታውቋል፡፡ በሁለቱም ሀገራት ድንበር ላይ የምትገኘው የኢትዮጵያዋ መተማ ከተማ፣ በየቀኑ ከ1000 በላይ ስደተኞችን እየተቀበለች እንደኾነችም መግለጫው አመልክቷል፡፡ከሱዳን ተሰድደው መተማ የሚደርሱት አብዛኞቹ ሰዎች፣ የደኅንነት ዋስትና ለማግኘት በሚያደርጉት ረዥም እና አደገኛ ጉዞ ምክንያት የተዳከሙ እንደኾኑ ድርጅቱ ገልጿል፡፡

የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ ቃል አቀባይ ኬ ቪራይ፣ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ መተማ ከደረሱት ስደተኞች መካከል፥ የሱዳን፣ የኢትዮጵያ፣ የቱርክ፣ የኤርትራ፣ የሶማሊያ እና የኬንያን ጨምሮ የ50 ሀገራት ዜጎች እንደሚገኙበት ጠቅሰው፣ አብዛኞቹ ግን ኢትዮጵያውያን እንደኾኑ አመልክተዋል፡፡

“መተማ ከደረሱት ስደተኞች አብዛኞቹ ወይም 39 ከመቶ የሚኾኑቱ ኢትዮጵያውያን ሲኾኑ፣ የሱዳን ዜጎች 17 ከመቶ፣ የቱርክ ዜጎች ደግሞ 13 ከመቶውን ይይዛሉ፤ በድምሩ እስከ አሁን ድረስ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ሰዎች ብዛት ከሁለት ቀናት በፊት 12 ሺሕ ደርሷል፡፡ ከጠቅላላው ስደተኛ 20 ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሕፃናት ናቸው፤” ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም፣ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ፣ ከ3ሺሕ500 በላይ ኢትዮጵያውያን ከሱዳን መውጣታቸውን፣ በትላንትናው ዕለት ገልጸዋል፡፡ የ61 ሀገራት ዜጎችም፣ በኢትዮጵያ በኩል መውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከሱዳን ወጥተዋል የተባሉት ኢትዮጵውያን፣ በምሥራቅ ሱዳን መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ያካተተ ስለመኾኑ ግን አልታወቀም፡፡

ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ካሉት ስደተኞች ውስጥ፣ በዚያች ሀገር የቆዩ ኢትዮጵያውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች እንደሚገኙባቸው፣ የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ቃለ አቀባይ ገልጸው፣ በዚኽ ላይ ዝርዝር መረጃ የሚኖረው ግን፣ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ ይህም ኾኖ፣ ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት፣ ከሁለት ዓመት በፊት ከትግራይ ተሰድደው በሱዳን መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ በሱዳኑ ግጭት ምክንያት ችግር ላይ መውደቃቸውንና የኢትዮጵያ መንግሥት በአፋጣኝ ደርሶላቸው ወደ አገራቸው እንዲመልሳቸው፣ በዚኽ ሳምንት የተማጽኖ ጥሪ ማቅረባቸው ተዘግቧል፡፡ ከሱዳን ተሰድደው መተማ የደረሱ ኤርትራውያን ደግሞ፣ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ መከልከላቸውን፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡ በሁለቱም ጉዳዮች ላይ፣ እስከ አሁን ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተሰማ ምላሽ ይኹን አስተያየት የለም፡፡

ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(አይኦኤም)፣ መተማ እየደረሱ ላሉት ስደተኞች ድጋፍ እንዲያደርግ፣ ከልዩ ልዩ ሀገራት ኤምባሲዎች ጥያቄ እየቀረበለት እንደኾነ፣ የድርጅቱ የኢትዮጵያ ቃል አቀባይ ኬ ቪራይ ተናግረዋል፡፡

“ልዩ ልዩ ኤምባሲዎች፣ ለዜጎቻቸው ድጋፍ እንድንሰጥ ጥያቄዎችን እያቀረቡልን ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ፥ የኬንያ፣ የሶማሊያ እና የዩጋንዳ መንግሥታት፣ ዜጎቻቸው ከድንበር ወደ ጎንደር ብሎም ወደ ዐዲስ አበባ የመጓጓዣ ድጋፍ እንድናደርግላቸው ጠይቀውናል፤” ብለዋል፡፡

በጥያቄውም መሠረት ድርጅቱ፣ ለ200 ኬንያውያን፣ ለ200 ዩጋንዳውያንና ከ800 በላይ ለኾኑ ሶማልያውያን ድጋፍ እንዳደረገላቸው ተናግሯል፡፡ ከዚኽም ባሻገር ድርጅቱ፣ መተማ ባለው ማዕከሉ አማካይነት፣ ለስደተኞቹ የምግብ እና የመጠለያ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

ስደተኞቹ፥ አስቸኳይ የውኃ፣ የምግብ፣ የመጠለያ፣ የንጽሕና መጠበቂያ፣ የሕክምና ርዳታ እና የመጓጓዣ አገልግሎት እንደሚፈልጉ ያመለከተው ድርጅቱ፣ ይህን ፍላጎት ለማሟላት፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል፡፡