በምግብ እና በሕክምና ዕጦት የተማረሩ የትግራይ ክልል የጦር ጉዳተኞች ለሦስተኛ ጊዜ ሰልፍ ወጡ

Your browser doesn’t support HTML5

የትግራይ ክልል የጦር ጉዳተኞች፣ የመሠረታዊ አገልግሎት አቅርቦት እንዲሟላላቸው በመጠየቅ፣ ትላንት ለሦስተኛ ጊዜ በመቐለ ሰልፍ አካሔዱ፡፡የምግብ አቅርቦቱ እና የሕክምና አገልግሎቱ እንዲሟላላቸው የጠየቁት ሰልፈኞቹ፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች፣ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ቅሬታቸውን በመቐለ ጎዳናዎች እየተዘዋወሩ ያሰሙት ጉዳተኞቹ፣ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ጋራ ተወያይተዋል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ ለጦር አካል ጉዳተኞቹ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሠራ፣ አቶ ጌታቸው ነግረዋቸዋል፡፡

“የመሠረታዊ አገልግሎት ጥያቄአችን መልስ አላገኘም፤” ያሉ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተዋጊዎች የነበሩ፤ የጦር አካል ጉዳተኞች፣ ትላንት ሰኞ፣ ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም.፣ በመቐለ ጎዳናዎች ላይ ሰልፍ አካሒደዋል፡፡

ከምሥራቅ መቐለ ከተማ ከሚገኘው ደጀን ወታደራዊ የሕክምና ማእከል ተነሥተው፣ ከ10 ኪ.ሜ. በላይ በእግር ተጉዘው ጥያቄአቸውን ያቀረቡት የጦር ጉዳተኞቹ፣ በቂ የምግብ አቅርቦት እና የሕክምና አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸውን በመጥቀስ አቤቱታቸውን በሰልፍ አሰምተዋል፡፡