“ህክምና ላይ እያለሁ መጀመርያ ላይ ሁለት ጊዜ በአይሮፕላን ድብደባ ተካሄዷል። አንዲት የሰባት አመት ዕድሜ ልጅ በአይሮፕላን ድብደባው ጭንቅላትዋ ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶባት ወደ ሆስፒታሉ መጥታ ነበር።አንድ የአራተኛ አመት የሶስዮሎጂ የዩኒቨርሲቲ ተማሪም ተመቶ ወድያውኑ ሁለቱ ሰዎች ሞቱ። ቅዳሜ ላይ መቐለን በተቆጣጠሩበት እለት ደግሞ መቐለ በከባድ መሳርያ ስትደበደብ ውላለች። ማለዳ ላይ፣ ቀንና ወደ ማታ ገደማ ብዙ የቆሰሉ ሲቪሎች ለህክምና መጥተው ነበር።
ዶክተር ፋሲካ መቐለ በከባድ መሳርያ መደብደብዋን ገልጸው፣ ስለሞቱትና ስለቆሰሉት ሰዎች አብራርተዋል።
“እኔ ያየሁት ወደ ዐይደር ሪፈራል ሆስቲታል ቆስለው የመጡት 40 ሰዎች ሲሆኑ የ 22 ሰዎች ግን አስከሬን ነው የመጣው። ልጆች፣ ወጣቶችና ወላጆች ይገኙባቸዋል። መቐለ ስትደበደብ በዋለችበት ወቅት መብራት ስለነበር የቻልነውን ያህል ልንረዳቸው ሞክረናል። ከዚያ በሁዋላ ግን መከላከያው ወደ ከተማይቱ ከገባ ከሶስት ቀናት በሁዋላ የኤለክትሪክ መብራት ተቋረጦ ሁሉ ነገር ተዘጋ። መድሃኒቱም አለቀ። ለመንቀሳቀስ በጣም ያስፈራ ስለበር ሰዉም ወደ ሃኪም ቤት መምጣቱን ተወው። ሁሉ ነገር እየተባባሰ ሄደ።”
ዶክተር ፋሲካ አምደ-ስላሴ ኢንሱሊንን የመሳሰሉት መድሃኒቶች ለወራት ያህል እንዳልነበሩ ገልጸው፣ አሁን ግን መድሀኒቶች ስለመጡልን፤ በቀይ መስቀል በኩል ዐድዋ ዶምቦስኮና ዐድግራትም ለማድረስ ችለናል ብለዋል።
ዶክተር ፋሲካ ይሰሩበት በነበረው ዐይደር ሪፈራል ሆስፒታል፣ የኤለክትሪክ መብራትና መድሃኒት ባልነበርበት ሁኔታ በህክምናው ስራቸው ስለገጠምዋቸው ተግዳሮቶች ዘርዝረዋል።
“ትልቁ ተግዳሮት የሰዉ ሞራልም ተነክቶ ነበር።መብራት ስላልነበረ ቁስል መቀየርያ አልነበረም። የምግብ አቅርቦት ቆመ። ምግብ ቤቱ ስለማይሰራ በሽተኞቹ ይራቡ ነበር። በሽተኞች ኦክሲጂናቸው አልቆ ሆስፒታሉ ውስጥ ሞተውብናል። ወደ ሁዋላ ዐይደር አከባቢ ያሉት ሰዎች ተደራጅተው ለበሽተኞቹ ብስኩትና ምግብ እያመጡ መርዳት ጀመሩ።”
ዶክተር ፋሲካ አሁን በትግራይ ክልል፣ ፈታኝ በሆነው ወቅት፣ የትግራይ ክልል ጊዚያዊ የጤና ቢሮ ሃላፊ ሆነዋል። በአሁኑ ወቅት እንዲህ አይነት ሃላፊነት መውሰድ ምን ያህል ተግዳሮታዊ ይመስሎታል? ለሚለው ጥያቄ፣
“እኔ አሁን ልምድ ኖሮኝም አይደለም። የህክምና ትምህርት ቤት አስተዳዳሪ ነው የነበርኩት። ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን የህክምናው ስራ መቀጠል አለበት። የደርሰበት ጉዳት አለ። ከዚህ በባሰ መልኩ ጥፋት እንዳይደርስበት ገብተን የማስተካከል፣ አገልግሎት የመስጠት ከሰዎች ጋር ግንኙነት የመፍጠር፣ ከፌደራሉ የጤና ሚኒስቴር፣ መንግስታዊ ካልሆኑ የረድኤት ድርጅቶችና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር ግንኙነት በመፍጠር መስራት አለብን። የጤናው ቢሮ ከደረሰበት ጉድት መነሳት አለብት። ስለሆነም በጣም ከባድ ቢሆንም ዩኒቨርሲቲው ሰዎች አቅርብ ተብሎ ሲጠቁምኝ ሰው የህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ የምችለውን መስራት አለብኝ በሚል መርህ ነው የተቀበልኩት።"
ዶክተር ፋሲካ ዐምደ-ስላሴ በአሁኑ ወቅት ስላለው የመድሀኒት አቅርቦት ሲያስረዱ፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሊረዳን በጣም ዝግጁ ነው። ቀይ መስቀልም እየርዳን ነው። መቐለ ላይ ወደ መደበኛ ሁኔታ ወደ መመለስ ተጠግተናል ብለዋል።
ችግሩ ግን ትግራይ ውስጥ ልንደርስ የምንችልባቸው ቦታዎች ጥቂት ናቸው። አክሱም ዐድዋ፣ ሽረና ቴምቤን ወደ መሳሰሉት ከተሞች ተደራሽነት የለንም ብለዋል ዶክተር ፋሲካ። በነዚህ ከተምች እንዴት መድሃኒት ማስገባት አለብን የሚለው ነገር እንደሚያሳሳባቸውም ዶክተር ፋሲካ ገልጸዋል።
ዐድግራትና ውቅሮ አከባቢ ያገኘናቸው ሃኪሞች፣ለሶስት ሳምንታት ያህል እሚያነጋግሩት ሰው እንኳን ሳይኖር፣ ብቻቸውን ስራ ላይ ተሰማርተው እንደቆዩ አይተናል ብለዋል ዶክተር ፋሲካ። ሂይወታቸውን ለማዳን ሳይሸሹ በስራ ገበታቸው መቆየቱን እንደመረጡ ነው የገለጹት።
ከመቐለ እስከ ዐድግራት ያለው አከባቢ ከባድ ውጊያዎች የተካሄዱበት በመሆኑ አሁን ምን አይነት ገጽታ አለው ለሚለው ጥያቄ፣
“ሰው የለም። ባለፍንባቸው ከተሞች ሁሉ እንቅስቃሴ አልነበረምd። ቤቶቹ ሁሉ ተዘግተዋል። ትልቅ ፍርሀት ሰፍኗል። የዐድግራት ሆስፒታልና የጤና ጣብያ እንዲሁም የውቅሮ ሆስፒታል ሁሉ ተዘርፏል። የጤና ጣብያዎቹና ሆስፒታሎቹ ባዶ ነው የቀሩት። የተቃጠሉ መኪኖችና ታንኮች ይታይሉ። አዲግራት የሚገኘው የመሃኒት ፋብርካም ሄጀ ባላየውም ሙሉ በሙሉ እንደተዘረፈ ነው የነገሩኝ። ዐድግራት ዩኒቨርሲቲም እንደተዘረፈና እንደወደመ ነግረውኛል።”
በመጨረሻም ዶክተር ፋሲካ ዐምደስላሴ፣ ድሮውም ቢሆን የኮቪድ 19 ቫይረስ ገጥሞት የነበረው የትግራይ ህዝብ፣ እሱ ባልፈጠረው ችግር መሰቃየት የለበትም ብለዋል። አለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች በምግብ፣ በመድሃኒት በማንኛውም በሚችሉት ነገር ሁሉ የትግራይን ህዝብ እንዲረዱም ጥሪ አቅርበዋል።
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5