የሊብያን አየር መንገድ አውሮፕላን ጠልፈው ዛሬ በሜዲተራኒያን ደሴት በማልታ ያሳረፉት ሁለት ሰዎች እጃቸውን ለፖሊስ መስጠታቸውን የማልታው ጠቅላይ ሚኒስትር ጆሴፍ ሙስካት አስታወቁ።
ጠ/ሚ በትዊተር መልዕክታቸው እንደገለፁት ጠላፊዎቹ የመጨረሻዎቹን ተሳፋሪዎች በሙሉ ለቀዋል።
ቀደም ሲል ግን አውሮፕላኑ ማልታ እንዳረፈ ወዲያውኑ ሕጻናትና ሴቶች እንዲወጡ ተፈቅዶላቸዋል።
ጠላፊዎቹ የአውሮፕላኑን አብራሪ አስቀርተው ቀሪዎቹን ተሣፋሪዎች ለመልቀቅ መስማማታቸውን የአየር መንገዱ ባለሥልጣናት ተናግረው እንደነበር ተዘግቧል።
ንብረትነቱ የመንግሥት የሆነው አፍሪቂያ አየርመንገድ አውሮፕላን መቶ አስራ ስምንት መንገደኞችን ይዞ ከሣብሃ ወደ ትሪፖሊ ከተማ በመብረር ላይ እያለ ነው ዛሬ አቅጣጫውን ወደ ማልታ እንዲቀይር የተገደደው።
ከጠለፋው በኋላ ወደ ማልታ የሚደረጉ ዓለምቀፍ በረራዎች በሙሉ ተሰርዘዋል።
የማልታ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጣሂር ሢያላ ሲናገሩ የጠላፊዎቹ ፍላጎት በሊቢያ አፍቃሪ ጋዳፊ የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት ነው።