ቁጥራቸው ወደዘጠና የሚሆኑ ደቡብ ኮርያውያን አረጋውያን ከሥልሳ ዓመት በላይ ከተለዩዋቸው ሰሜን ኮሪያ ከሚኖሩ ዘመዶቻቸው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኙ።
ዋሺንግተን ዲሲ —
ቁጥራቸው ወደዘጠና የሚሆኑ ደቡብ ኮርያውያን አረጋውያን ከሥልሳ ዓመት በላይ ከተለዩዋቸው ሰሜን ኮሪያ ከሚኖሩ ዘመዶቻቸው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኙ።
ዛሬ ሰኞ ደቡብ ኮሪያዋያኑን ያሳፈሩት አውቶቡሶች ከሰዓታት በኋላ የሰሜኑዋን ድንበር አቋርጠው ኮሪያዋ ካማንግ ተራራ የመዝናኛ ስፍራ ሁለቱ ወገኖች ሲገናኙ ተቃቅፈው ሲላቀሱ ተስተውሏል።
የኮርያ ልሳነ ምድርን ሁለት ላይ ከከፈለው ጦርነት ወዲህ ሲገናኙ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ሲሆን በቀጣዮቹ ሦስት ቀናት የሰሜን ኮርያ የደኅንነት ሰዎች በዓይነ ቁራኛ እየተከታተሏቸው ከዘመዶቻቸው ጋር ሥድስት ጊዜ በአካል ተገናኝተው ጊዜ እንደሚያሳልፉ ተገልጿል።
እኤአ ከ2000 ወዲህ እንዲህ ዓይነት የዘመዶች መገናኘት መርኃ ግብር ሲከናዎን ሃያኛ ጊዜ መሆኑ ተጠቁሟል።
እኤአ ከ1950 እስከ 1953 በተካሄደው ጦርነት በሚሊዮኖች የተቆጠሩ ቤተሰቦች ተለያይተዋል። ይህ ከሆነ ከሃምሳ ዓመት በላይ በማለፉም ብዙዎች ከቤተሰቦቻቸው ሳይገናኙ አልፈዋል፤ በህይወት ያሉት አብዛኞቹም ከሰማኒያ ዓመት በላይ ናቸው ።