በኅዳሴ ግድብ ጉዳይ ላለፉት ሦስት ቀናት የመከሩት ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን እንዲሁም ዩናይትድ ስቴትስና የዓለም ባንክ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ሚኒስቴር የሕዝብ ጉዳዮች ቢሮ ዛሬ ባሠራጨው መግለጫ የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ልዑኮቻቸው በታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ አሞላልና ሥራ ላይ ከጥር 19/2012 ዓ.ም. እስከ ዛሬ ጥር 22/2012 ዓ.ም. ዋሺንግተን ዲ.ሲ. ውስጥ ባደረጉት ድርድር ላይ በታዛቢነት እየተሣተፉ ካሉት የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ሚኒስትር እና የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ጋር መገናኘታቸውን አስታውቋል።
በስብሰባዎቻቸው ማብቂያ ሚኒስትሮቹ በአጠቃላይ ስምምነቱ መፈረም ባለባቸው ሦስት ነጥቦች ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አመልክቷል።
ነጥቦቹም አንደኛ፣ የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ደረጃ በደረጃ አሞላል የጊዜ ሰሌዳ፤ ሁለተኛ፣ በድርቅና በተራዘመ ድርቅ ጊዜና በተራዘሙ ደረቅ ዓመታት ወቅት የግድቡ አሞላል ቅነሳ ሥርዓት፤ እንዲሁም ሦስተኛ፣ በድርቅና በተራዘመ ድርቅ ጊዜና በተራዘሙ ደረቅ ዓመታት ግድቡን የማንቀሳቀስ ዓመታዊና የተራዘመ ጊዜ ቅነሳ ሥርዓት መሆናቸውን የጋራ መግለጫው አመልክቷል።
በተጨማሪም ሚኒስትሮቹና ልዑኮቻቸው በመደበኛው የእርጥበትና የውኃ ግኝት ሁኔታዎች ውስጥ በግድቡ ዓመታዊና የተራዘመ ጊዜ የማንቀሳቀስ ሥርዓት ዝግጅት ማጠናቀቅ ላይ እንዲሁም በቅንጅት ሥርዓት፣ በውዝግብ አፈታት ደንቦችና በመረጃ ልውውጥ ላይ መወያየታቸውንና መስማማታቸውንም መግለጫው ጠቁሟል።
በተጨማሪም ለግድቡ ደኅንነትና ለተንጠለጠሉ የተፈጥሮ አካባቢና የማኅበራዊ ጫና ጥናቶችም መፍትኄ ለመስጠት መስማማታቸውም በጋራ መግለጫው ተጠቁሟል።
ከላይ የተጠቀሱትን ስምምነቶች ያካተተ የመጨረሻ የሥምምነት ሰነድ ለፌብርዋሪ 2020 ዓ.ም. መጨረሻ (የካቲት 2012 ዓ.ም. የመጨረሻ ሣምንት) እንዲያዘጋጁ ሚኒስትሮቹ ለቴክኒክና ለህግ ቡድኖቻቸው ትዕዛዝ መስጠታቸውንም መግለጫው አስታውቋል።
ወሰን ተሻጋሪ ትብብርን፣ አካባቢያዊ ልማትና ምጣኔ ኃብታዊ መቀናጀትን ግምት ውስጥ ባስገባ ሁኔታ ከስምምነቱ የሚመነጩ ጉልህ አካባቢያዊ ጥቅሞችን ሚኒስትሮቹ እንደሚገነዘቡ ወይም ዕውቅና እንደሚሰጧቸው አመልክቷል የአምስቱ ወገኖች የጋራ መግለጫ።
ጥቁር አባይን በማልማት የኢትዮጵያን፣ የግብፅንና የሱዳንን ሕዝቦች ሕይወቶች ለማሻሻል የወሰን ተሻጋሪ ትብብርን አስፈላጊነት ሚኒስትሮቹ በድጋሚ ማረጋገጣቸውን የጋራ መግለጫው አመልክቷል።