የሰሞኑን የተለያዩ የጤና መረጃዎችና ጥቃቅን እውነታዎች ያዳምጡ፡፡
Your browser doesn’t support HTML5
ኢትዮጵያ ውስጥ የማጅራት ገትር ወረርሽኝ መቀስቀሱን የዓለም የጤና ድርጅት ሰሞኑን አስታውቋል፡፡
ከመጋቢት እስከ እስከ ሚያዝያ መጨረሻ ወይም ግንቦት መጀመሪያ ያለው ጊዜም ከፍተኛ የመተላለፍ መጠን የሚኖርበት ጊዜ እንደሆነም ድርጅቱ ገልጿል፡፡
ለማጅራት ገትር ተጋልጠዋል የሚባሉ ሕሙማን በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ ሲሆን በሁለቱም ክልሎች ውሰጥ በሚገኙ 14 ዞኖች ውስጥ በስድሣ ወረዳዎች መስፋፋቱም ታውቋል፡፡ በተለይ በ16 ወረዳዎች ውስጥ ግን ወረርሽኙ በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ማጅራት ገትር እየተስፋፋባቸው መምጣቱን ካስታወቁት አካባቢዎች መካከል አርባምንጭ ዙሪያ፣ ሃላባ፣ ሃዋሣ ከተማ፣ ዳሌ፣ ሸበዲኖ፣ ጎርቼ እና ወንሾ በደቡብ፣ እንዲሁም አርሲ ነገሌ፣ ሻላ፣ ሻሸመኔ ከተማ እና የሻሸመኔ የገጠር አካባቢዎች፣ ዶዶላ፣ ሲራሮ፣ ወንዶ እና ገደብ አሣሣ በኦሮሚያ ክልል ይገኛሉ፡፡
ከባለሙያች የሚሰጥዎን ምክር ይጠብቁ፤ እራስዎንና ቤተሰብዎን ይጠብቁ፡፡
ወባ እጅግ ገዳይ ከሚባሉ ጅምላፈጅ ወረርሽኞች አንዱ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ወባ በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ሕይወት የሚያጠፋ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ግን ምቹ የሆነ የማኅበራዊ ጤና ችግር ነው፡፡ወባ በተለይ በእናቶችና ዕድሜአቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን በስፋት ስለሚያጠቃ ከሚያደርሰው ማኅበራዊ ቀውስ በተጨማሪ የሥነ-ሕዝብ መመሣቀልና መዛባትንም እንደሚያስከትል አጥኚዎች ይናገራሉ፡፡
በአዋቆች ዘንድም ዕድሜአቸው በቀልጣፋ የምርት ዘመን ላይ ሆነው በምርት ወቅት ስለሚጥላቸው የምግብ ቀውስ እና የምጣኔ ኃብት መዛባትን የሚያደርስ፣ በተለይ በገጠር ቤተሰቦች ላይ ድህነትን የሚያስከትልና የሚያባብስ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ በአንጋል ሴሎች መላሸቅ ምክንያት የሚከሰተውን የፓርኪንሰን ሕመም እየተባለ የሚጠራውን የሰውነት አካላት በተዋሃደና በተናበበ ቅልጥፍና መንቀሳቀስ እንዲሣናቸው የሚደርገውን የጤና ችግር ለማከም አሁን እየተሰጡ ካሉ ሕክምናዎች የተሻለ ዘዴ እየተገኘ መሆኑን ተመራማሪዎች እየተናገሩ ነው - መልካም ዜና ይሰማል፡፡
አራስ ሕፃናት ለበሽታዎችና በተሃዋስያን ለመመረዝ ከማንም በላይ የተጋለጡ ናቸው፡፡ አሁን ታዲያ ለበዙ የበሽታ ዓይነቶች እንዳይጋለጡ የሚከላከልላቸው አዲስ ዓይነት ውሁድ ክትባት ተሠርቷል፡፡
ይህ ውሁድ ሌሎች ዓይነት ክትባቶችም በተሣካ ሁኔታ እንዲሠሩና የሰውነት የተፈጥሮ የመከላከል አቅም በብዙ እንዲጎለብት የሚያስችል ነው፡፡ በዓለም ዘሪያ ለዕልቂት ለተጋለጡ ለሚሊዮኖች ሕፃናት መድኅን ሊሆን ነው - ይህ አዲስ ክትባት፡፡ - ሌላ መልካም ዜና፡፡
ጤናዎን ይጠብቁ፤ የግልዎ ፅዳት፣ የአካባቢዎ ንፅሕና፣ አመጋገብዎና ተከታታይ እንቅስቃሴ ከኪኒንና ከመርፌ ያርቁዎታል፡፡
ስለጤናዎ፣ ስለአመጋገብዎ፣ ስለራስዎና ስለቤተሰብዎ ደህንነት፣ ስለሚያስጨንቁዎ የጤና ጉዳዮች አጠገብዎ የሚያገኙትን የጤና ባለሙያ ከማማከር አይቦዝኑ፤ ደግሞም እጅዎን ያለመታከት ቢያንስ ለሃያ ሰከንዶች ያህል ይታጠቡ፣ እጆችዎን ለመታጠብ ጊዜና አጋጣሚውን ባገኙ ቁጥር ይታጠቡ፤ እጆችዎ ከውኃና ከሣሙና ከራቁ መቼም ንፁህ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በሽታዎችን ሃምሣ ከመቶ ለሚሆን መጠን እጀችዎን በሣሙና በመታጠብ ሊያስወግዱ እንደሚችሉ እባክዎ ያጢኑ፡፡ ከጤናዎ በላይ ምን ኃብትና የሚጠብቁት ንብረት አለዎ? ጤናዎን በተቻለዎ አቅም እና በተቻለዎ ዘዴ ሁሉ ይጠብቁ፣ ከከበቡዎ ጠላቶችዎ ወረራና ጥቃት ይጠብቁ፣ በራስዎ ብቸኛው ወታደር እርስዎ ብቻ ነዎትና፡፡ ከጠፉም አጥፊው በቅድሚያ እራስዎ ነዎ - መቼም በዚህ እንግባባለን፤ አይመስልዎትም?
ደግሞም ጥርሶችዎን ያለመታከት ቢያንስ በቀን ሁለት ጊዜ ያፅዱ፤ ጤናማ፣ ጠንካራና ጠረን አልባ ጥርሶችዎን እኮ ለአጠቃላዩ ጤናዎ፣ ደግሞም ለውበትዎ፣ ደግሞም ለማኅበራዊ ሕይወትዎም ይፈልጓቸዋል፡፡ አይደል?
ከዚህ ጋር የተያያዘው የድምፅ ፋይል ሌሎችም ዝርዝር ቁምነገሮችን ይዟል፡፡ ያዳምጡት፡፡ - ቪኦኤ-አፍሪካ የጤና አውታር፡፡