በጀርመን አንጌላ መርከልን ማን እንደሚተካ የሚወስነው የፓርላማ ምርጫ ተካሄደ

ቻንስለር አንጌላ መርከል እና የክርስቲያን ዲሞክራቶች አንድነት ፓርቲያቸው ዕጩ አርሚን ላሼት

ለአስራ ስድስት ዐመት ጀርመንን የመሯትአንጌላ መርከል ይሰናበታሉ። የህዝብ አስተያየቶች መርከልን ለመተካት የቀረቡት ዕጩዎች ብርቱ ፉክክር ላይ መሆናቸውን አሳይተዋል።

ስድሳ ሚሊዮኑ የጀርመን ብቁ መራጭ ዛሬ አዲስ የምክር ቤት አባላቱን ሲመርጥ ውሏል። የዚህ ምርጫ ውጤት በአውሮፓ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ የሆነችውን ሃገር ለአስራ ስድስት ዐመት የመሩዋትን አንጌላ መርከልን ማን እንደሚተካ ይወስናል።

በአርሚን ላቼት የሚመራው ቀኝ ዘመሙ የመርከል ክሪስቲያን ዲሞክራቶች አንድነት ፓርቲ እና በተሰናባቹ ምክትል ቻንስለር ኦላፍሾልዝ የሚመሩት ግራ ዘመሞቹ ሶሻል ዲሞክራቶች እጅግ ተቀራራቢ በሆነ የመራጭ ድጋፍ በብርቱ ፉክክር ተጣምደዋል።

በቅርቡ በወጡ የመራጭ አስተያየት ግምገማዎች መሰረት ሶሻል ዲሞክራቶች በጥቂት የድምጽ ብልጫ እየመሩሲሆን የተፈጥሮ አካባቢ ደህንነት ተሙዋጋቹ ግሪንስ ፓርቲ እና መሪያቸው አናሌና ቤርቦክ በሶስተኛነት ይከተላሉ።

የሚመረጡት የምክር ቤት አባላት ጥምር መንግሥት ማቋቋም ሳይኖርባቸው እንደማይቀርእየተገለጸ ሲሆን ከዚያም ተያይዞ መርከልን ማን እንደሚተካ የመወሰኑም ሂደት ሳምንታት ሊወስድ ይችላል። በአሰተያየት ግምገማዎች መሰረት ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያላቸው ከሰላሳ ከመቶ ያነሰ የመራጭ ድጋፍ በመሆኑ ማናቸውም አብላጫ ድምጽ ያገኛሉ ተብሎ አይጠበቅም።

አንጌላ መርከል ሊተኩዋቸው ከሚፎካከሩት ዕጩዎች ውስጥ ለአንዳቸውም በይፋ ድጋፋቸውን ከመግለጽ ተቆጥበው ከርመዋል። ትናንት ግን ለክሪስቲያን ዲሞክራት ፓርቲው ዕጩ አርሚን ላሼት በተደረገ የድጋፍ ስብሰባ ላይ ተገኝተዋል። መርከል ተተኪያቸው እስከሚመረጥ በተጠባባቂ ቻንስለርነት ይቆያሉ።