ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ የውጭ ሀገር ሕክምና በመከልከላቸው ሕመማቸው እየተባባሰ እንደኾነ ገለጹ

Your browser doesn’t support HTML5

· ባለቤታቸው፣ “ክሥ ለመመሥረት እየተዘጋጀን ነው፤” ብለዋል

ከአራት ወራት በፊት ወደ ውጭ ሀገር ሔደው እንዲታከሙ የሐኪሞች ቦርድ ቢያዝም፣ መንግሥት ፈቃደኛ ባለመኾኑ የጤና እክላቸው እየተባባሰባቸው እንደኾነ የቀድሞው የአማራ ክልል ልዩ ኀይል ዋና አዛዥ የነበሩት ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ ተናገሩ። ጀነራሉ፣ በወቅቱ ሕክምና ባለማግኘታቸው፣ በአሁኑ ሰዓት በጽኑ ታመው አልጋ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ባለቤታቸው ወ/ሮ መነን ኀይለ በበኩላቸው፣ ለሕክምና ወደ እስራኤል ለመጓዝ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ፣ የመሳፈርያ ቅጹ ላይ ይለፍ የሚል ማኅተም የሚያደርገው ግለሰብ፣ ከበላይ አካል የመጣ ትእዛዝ ነው፤ በማለት እንደ ከለከሏቸው ገልጸዋል፡፡ የከለከለውን አካል ለማወቅ ጥረት ቢያደርጉም እንዳልተሳካላቸውና በቅርቡም ክሥ እንደሚመሠርቱ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

በ1980 ዓ.ም የደርግ ሥርዐተ መንግሥት ሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት፣ በቀኝ እግራቸው ላይ ያልወጣ ጥይት እና የቦንብ ፍንጣሪ እንዳለ በሐኪሞች በመረጋገጡና ወደ ውጭ ሀገር ሔደው እንዲታከሙ በሐኪሞች ቦርድ መወሰኑን የጠቀሱት ጀነራሉ፣ ባለፈው ኅዳር ወር፣ ከሀገር መውጣት እንዳይችሉ በመንግሥት መከልከላቸውን ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ ሕክምና ማግኘት ሲገባቸው ባለማግኘታቸው፣ ሕመሙ እየባሰባቸው እንደ መጣ ገልጸዋል፡፡

“ለብዙ ጊዜ የኖሩ ተደጋጋሚ ምቶች እዚያው ውስጥ አሉ፤ ነገር ግን በየጊዜው ሕክምና አላገኘኹም፡፡ በሀገር ውስጥ ለመታከም ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጌ፣ ይህ በውጭ ካልኾነ በሀገር ውስጥ አደጋ ይገጥምሃል፤ ከነርቭኽ ጋራ የተያያዘ ነገር አለው እግርኽ ላይ አደጋ ሊገጥምኽ ይችላል፤ አሉኝ፡፡ እኔም የሰጋኹት እርሱን ነው፤ ምክንያቱም የተሰገሰገው በእርሱ ውስጥ ነው።” ብለዋል። ቀኝ እግራቸው እንዳይንቀሳቀስ ሊከለክላቸው እንደሚችል ስጋት እንዳላቸው የገለፁት ጀነራሉ “የሐኪሞችም ስጋታቸው፣

ይህ በወቅቱ መታከም አለበት፤ አላስፈላጊ ጊዜ እየወሰደ ነው፤ የሚል ነው፤ የእኔም ስጋቴ ይህ ነው፡፡” ብለዋል።

ባለቤታቸው ወ/ሮ መነን ኀይለ እንደሚሉት፣ የባለቤታቸው የውጭ ጉዞ የተሰረዘው፣ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከበላይ በመጣ አካል በመጣ ትእዛዝ ነው፤ በሚል ምክንያት እንደኾነ ገልጸው፣ በእነማን ነው የተከለከለው የሚለውን ለማወቅ ጥረት ማድረጋቸውንና እንዳልተሳካላቸው ተናግረዋል፡፡ ችግሩ የቱ ጋራ እንዳለ ባለማወቃቸው፣ ጉዳዩን ወደ ሕግ ለመውሰድ በዝግጅት ላይ እንደኾኑ አክለው ገልጸዋል፡፡

“የእስራኤል ኤምባሲ የክብር ቪዛ ነው የሰጡት፡፡ ትኬት ቆርጠን ቀጥታ የሔድነው ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ነው፡፡ በአየር ማረፊያው፣ ሚዛን ተለክተን ኹሉንም አልፈን ከጨረስንና ይለፍ ከተመታ በኋላ፣ ማኅተም ያደረገው ሰው፣ ስልክ ተደዋውሎ ከተነጋገረ በኋላ፣ “ቀርተዋል” ብሎ ጻፈበት በእስክሪቢቶ፡፡ ማን ነው ያለው ስንለው፣ “ከበላይ አካል ነው” አለን፡፡ የበላይ አካል ማን ነው? ስንለው፣ “ወደ ኢሜግሬሽን ሔዳችኹ ጠይቁ” አለን፡፡ እዚያ ሔደን ስንጠይቅ፣ “እኛ አልከለከልናቸውም” አለን ሓላፊው፡፡ በዚያ ሰዓት ወደ 200 ሺሕ ብር ነው ያወጣነው፡፡ እንግዲህ አሁን እኛ መጀመሪያ የከለከለን አካል ይታወቅልን ብለን ክሥ ልንጀምር ነው።”

ብርጋዴል ጀነራል ተፈራ ማሞ፣ ባለፈው ዓመት፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኀይል ለመናድ ሞክረዋል፤ በሚል ወንጀል ተከሠው፣ ጉዳያቸው በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲታይ የነበረ ሲኾን፤ ኋላም በ30ሺሕ ብር ዋስ መለቀቃቸው ይታወሳል፡፡

በዚያ ወቅት የሕግ አማካሪያቸው እና ጠበቃቸው የነበሩት ሸጋው አለበልን፣ ጀነራሉ ያላለቀ የክሥ ሒደት እንዳላቸው ጠይቀናቸው፤ “ጀነራል ተፈራ ማሞ፣ በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ነው ስንከታተልላቸው የነበረው፡፡ ከዚያ በኋላ የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡ አልቆ፣ የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸው ወጥተዋል፡፡ ይህ ከኾነ በኋላ፣ በእርሳቸው ላይ የቀረበ አንዳችም የወንጀል ክሥ የለም፡፡ እስከ አሁን ድረስ እየተካሔደባቸው ያለ ክትትል ባለመኖሩ፣ በሕግ ይፈለጋሉ፤ የሚያሰኝ ምክንያት የለም፡፡” ብለውናል።

ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት፣ ከመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት እና ከፍትሕ ሚኒስቴር እንዲሁም፣ ከአማራ ክልል መንግሥት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፡፡

ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር በፊት በነበረው ሥርዐተ መንግሥት፣ “መፈንቅለ መንግሥት ለማካሔድ አሢረዋል፤” በሚል በእስር ላይ የቆዩ ሲኾን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ ከእስር ተለቀው፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ኾነው አገልግለዋል፡፡ ከልዩ ኃይል አዛዥነታቸው ተነሥተው፣ ለክልሉ ርእሰ መስተዳደር የአማካሪነት ሹመት ቢሰጣቸውም ሳይቀበሉት መቅረታቸው ይታወሳል። በተጨማሪም በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን ኾነው በውጊያ መሳተፋቸው ይነገራል።